Search

የኢትዮጵያ ዕድገት በመደመር መንግስት ዐይን

ረቡዕ ሐምሌ 01, 2018 92

የኢትዮጵያን አጠቃላይ ዕድገትና ጥንካሬ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ፓርላማ ውሏቸው  ያነሱት ሀሳብ፣ "የመደመር መንግስት" ከተሰኘው  የፍልስፍና እና የስርዓት ግንባታ እሳቤ ጋር በቀጥታ የሚተሳሰር ነው። የመደመር መንግስት የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የተቀየሰ ስርዓት ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ደግሞ ይህ ስርዓት በተግባር ያመጣቸውን ውጤቶች የሚያሳይ ነው።

1. ከመደመር እሳቤ አኳያ የሀገር ዕድገት ምን መምሰል አለበት? የመደመር መንግስት የዕድገት እሳቤ ዋነኛ ማዕከል "ፈጠራና ፍጥነት" ነው። የኋላ ቀርነት አዙሪትን ለመስበር የተለመደውን አዝጋሚ ጉዞ መተውና እመርታዊ ለውጥ (ክሥቱነት) ማምጣት እንዳለበት የመደመር እሳቤ ያስረዳል። ዕድገቱ የባከነውን ጊዜ የሚያካክስ፣ ፈጣን፣ ፍትሐዊና ዘላቂ መሆን ይኖርበታል።

ይህንንም ለማሳካት መንግስት "የዝላይ ስልትን" (Leapfrogging Strategy) በመጠቀም፣ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር እንዲሁም በመፍጠን ከበለጸጉት ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ መስራት አለበት። ዕድገቱ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ትብብር ላይ የተመሰረተ "ሥርዓታዊ ፍጥነት" (Systemic speed) ሊኖረው ይገባል።

2. የመደመርን የዕድገት ተልዕኮ መንግስት እንዴት ፈጸመው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የመደመር መንግስትን የዕድገት እና የፍጥነት እሳቤ መንግስታቸው እንዴት በተግባር እንደፈጸመው በዝርዝር አብራርተዋል። ሀገሪቱ ያጋጠማትን ዘርፈ ብዙ አለም አቀፍና ሀገር በቀል ተግዳሮቶች ተቋቁማ ከ10.2 እስከ 10.3 በመቶ የሚደርስ የኢኮኖሚ እድገት ማምጣቷን፣ ይህም በአፍሪካ ትልቁ ዕድገት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የመደመርን የዝላይ ስትራቴጂ እና ፍጥነት በሚያረጋግጥ መልኩ፣ የዘንድሮው የኤክስፖርት 11 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ይህም ከ1984 እስከ 2000 ዓ.ም ባሉት 17 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ካገኘችው አጠቃላይ የኤክስፖርት ገቢ ጋር በአንድ አመት ብቻ እኩል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። በተጨማሪም ከቡና 3.1 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ከወርቅ ወደ 5.5 ቢሊዮን ዶላር ኤክስፖርት መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

3. የማክሮ ኢኮኖሚ ጥንካሬ እና የትብብር ስኬት የመደመር መንግስት እሳቤ የማይበገር እና ጫናዎችን የሚቋቋም (Resilient) ኢኮኖሚ መገንባትን ያልማል። ይህን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከነበረበት መጠን ከ20 እጥፍ በላይ አድጓል። መንግስት ላለፉት 8 ዓመታት ምንም አይነት የንግድ ብድር (Commercial loan) አለመውሰዱንና የዕዳ ሽግሽግ በማድረግ ሀገራዊ የብድር ጫናውን ከ50 በመቶ በታች ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የበጀት ጉድለቱን ከ1.2 በመቶ በታች በማድረግ ጤናማ በሆነ የግምጃ ቤት ሰነድ መሸፈኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

4. የስራ እድል እና መዋቅራዊ ሽግግር በመደመር መንግስት የትብብር ሞዴል መሰረት ሀብት የሚፈጥር ማህበረሰብ መገንባት ዋነኛ ግብ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው እንደገለጹት፣ ዘንድሮ በሀገር ውስጥ፣ በውጭ ሀገር ስምሪት እና በርቀት (Remote) ስራ በአጠቃላይ ከ5 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ እድል አግኝተዋል።

የግብርናው ዘርፍ 7.7 በመቶ እድገት በማሳየት 1.3 ቢሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። በኢንዱስትሪው ዘርፍም 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

በአጠቃላይ፣ ከመደመር መንግስት የፍጥነት፣ የፈጠራ እና አቋራጭ የዝላይ መንገድ አኳያ ሲታይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የሚያሳየው መንግስት እሳቤውን በተግባር በመተርጎም ኢትዮጵያን ወደ ተጨባጭ ሁለንተናዊ ብልጽግና እያመራት መሆኑን ነው።

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ