Search

የመከሩ ሀገር አኖሩ!

ሓሙስ ሐምሌ 02, 2018 160

ለኢትዮጵያዊያን ሀገር መገንባት አዲስ ነገር አይደለም። የታሪክ መዛግብት ሲገለጡ የኢትዮጵያ ስም ከጥንታዊ ሥልጣኔዎች አንዱ ሆኖ ይነበባል። እኛ ኢትዮጵያዊያን የመንግሥት አሥተዳደር መሥርተን፣ ሕግና ሥርዐት አበጅተን፣ በሃይማኖት ታንጸን፣ በጀግንነት ሀገር ጠብቀን፣ በሥነጽሑፍ ተጠብበን፣ ማኅበራዊ ቁርኝታችንን አጥብቀን ለሺህ ዘመናት የኖርን የታላቅ ሀገር ዜጎች ነን። ታሪካችን ሲነበብ እልፍ አኩሪ ገድሎች ይዘረዘራሉ። የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲልነታችን ብቻውን ማንነታችን ከድል፣ ከክብርና ከእፁብ ድንቅ እሴቶች የተሸመነ መኾኑን ይመሰክራል።

በረዥሙ የሀገርነት ታሪካችን የተፈጠሩ የሀሳብ አለመግባባቶች ግን አንድ ቦታ ላይ ያልተጠገነ ስብራት ፈጥረውብናል። ይኸውም ልዩነቶችን በኃይል የመፍታት ልማድ ነው። ከጠመንጃ አፈሙዝ ሥልጣንን ለማመንጨት የተጓዝንባቸው መንገዶች ክፉኛ አቁስለውናል። ትርክቶች ሥር ሰድደው አጋጭተውናል። ሰላማዊ የፖለቲካ ውይይት ባለመዳበሩ እርስ በእርስ ለመሸናነፍ ተማምለን ማንንም ሳይሆን ራሳችንን ጎድተናል። ሀገራዊ ምክክር ብቸኛው ዘላቂ የሰላም ጎዳና ስለመኾኑ በተለያዩ ጊዜያት በሀገር ወዳድ ዜጎች ምክረሀሳብ ቢቀርብም ሰሚ ጆሮ ሳያገኝ ያለመግባባት መንስኤዎች ተጠናክረው ቀጥለውም ነበር።

እነሆ አሁን ኢትዮጵያ እየመከረች ነው። ልጆቿ ከአራቱም አቅጣጫ ተሰባስበው ለዘመናት የዘለቁ ያለመግባባት መንስኤዎችን ለማከም ቀን ቆርጠው እየጠበቁ ነው። ሀገር መገንባት፣ ትውልድ ማሻገርና እሴት ማስቀጠል የሚያውቁት ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን በምክክር ለማጽናት ተዘጋጅተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች ሀገር የተሸረሸሩ መልካም እሴቶቿን የምታድሰው በምክክር መኾኑን በተግባር ሊያሳዩ በመዲናቸው እየተሰባሰቡ ነው፡፡

 

በመመካከር ኹላችንም እናሸንፋለን፡፡ በመመካከር መግባባትን እንፈጥራለን፡፡ በመመካከር ያልሻሩ ቁስሎችን እናክማለን፡፡ ይህን ጠንቅቀው የተገነዘቡት ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን ዳግም በዓለም ፊት አብሪ ኮከብ ለማድረግ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን እየተጠባበቁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች ዛሬም ሀገራቸው ባለመግባባት ሕመም መቸገሯን ሊያክሙ የመፍትሔ ሀሳባቸውን አዘጋጅተዋል፡፡

ግጭት ሀገርን ያፈርሳል፡፡ መቃቃርን ያባብሳል፡፡ ሰላምን እንዳትመለስ አድርጎ ያሸሻታል፡፡ ሀገር በዘላቂነት ሰላም የምትፈጥረው፣ ማኀበራዊ ቁርኝት የሚጠናከረውና ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠረው በምክክር ብቻ ነው፡፡

በምክክር ሀገራዊ መግባባት እንፍጠር፤ ኢትዮጵያን ለትውልድ እናሻግር!

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን!