ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ በርካታ ታላላቅ ድሎችን ያስመዘገበች ቢሆንም፣ በሂደት ውስጥ ግን በርካታ ውጣ ውረዶችን፣ የሐሳብ ግጭቶችን እና መዋቅራዊ የፖለቲካ አለመረጋጋቶችን አሳልፋለች።
እነዚህን ተግዳሮቶች በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ "በውይይት ብቻ የምትጸና ሀገር" የሚለው መርህ አማራጭ የሌለው የሕዝብ ተስፋ እና የኅልውና ጉዳይ ሆኗል።
የሀገረ መንግሥት ግንባታ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የሀገር ፅናት የሚለካው በወታደራዊ ኃይል ሳይሆን በዜጎች መካከል በሚኖር የጋራ መግባባት ላይ ነው።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ለሰለጠነ ፖለቲካ እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ብቸኛው አስተማማኝ ድልድይ ነው።
ይህ ሀገራዊ ምክክር ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ለሰለጠነ ፖለቲካ እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ብቸኛው አስተማማኝ መንገድ መሆኑን በተግባር የሚያሳይ ነው።
ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችለውም የችግሮቹን መንስኤ በጠረጴዛ ዙሪያ በሀቀኝነትና በግልጽነት በመወያየት ብቻ ነው።
ምክክሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና የሐሳብ መሪዎች በነጻነት የሚደማመጡበት መድረክ በመፍጠር፤ ቂምና ቁስሎችን በይቅርታና በውይይት በማከም፣ የጦርነትና የንትርክን ምዕራፍ ዘግቶ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ዋነኛው መፍትሄ ነው።
የሰለጠነ ፖለቲካ መገለጫው ልዩነትን በሐሳብ የበላይነት ማሸነፍ፣ የሌላውን ወገን ስጋትና ፍላጎት መረዳት እና በጋራ ጉዳዮች ላይ መስማማት ነው።
ይህ ምክክር የሀገራችንን የፖለቲካ ልሂቃን ከሴራ ፖለቲካ አውጥቶ በሐሳብ ፍልሚያና በሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የሰለጠነ ባህል እንዲያዳብሩ ያግዛል።
አንድት ጠንካራ ሀገር ልትገነባ የምትችለው በዜጎቿ የጋራ ስምምነት ላይ ስትመሰረት ብቻ ሲሆን፣ በምክክሩ አማካኝነት በዋና ዋና ብሔራዊ መግባቢያ ጉዳዮች፣ በታሪክ ትረካዎች እና በጋራ እሴቶች ላይ የጋራ መግባባት ይደረሳል።
ይህም ሕዝቡ በሀገረ መንግሥቱ ግንባታ ላይ እኩል ባለቤትነት እንዲሰማው ስለሚያደርግ፣ ወደፊት የሚመጡ መንግሥታት ጠንካራ፣ ህጋዊና በሕዝብ እምነት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ መሰረት ይጥላል።
"በውይይት ብቻ የምትጸና ሀገር" የሚለው መርህ የኢትዮጵያን ዘርፈ-ብዙ እና ውስብስብ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የተመረጠ ብቸኛው የሰላም መንገድ ነው።
ሂደቱ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ማለትም ከመንግሥት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰቡ እና ከእያንዳንዱ ዜጋ ከፍተኛ ቅንነት፣ ግልጽነት እና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይፈልጋል።
ኢትዮጵያ ወደ አዲሱ ከፍታ የምትሻገረው ልዩነቶቿን ውበት፣ ውይይቷን ደግሞ መመሪያዋ ስታደርግ ብቻ ነው።
በሔዋን ጌታቸው