Search

ቀይ ባህር፤ የጋራ ቋንቋችን!

ረቡዕ ሐምሌ 01, 2018 182

ቀይ ባህር ታሪካችን፣ ትዝታችን፣ ከጥንት ስልጣኔያችን ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ  ኢትዮጵያን ከቀሪው ዓለም ጋር ያስተሳሰረ የደም ስራችን፣ እንዲሁም የንግድና የዲፕሎማሲ በራችን ነው።

ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ የፈጠረ፣ የማንነታችን ታሪካዊ ማህተም እና የኢትዮጵያውያንን ዓለም አቀፍ ዝና በታሪክ ማህደር ውስጥ ጠልቆ የተከለ ውድ ሀብታችን ነው። ለኢትዮጵያውያን ቀይ ባህር የስም አጠራር ብቻ ሳይሆን፣ ትርጉሙ እጅግ የገዘፈ፣ የሕልውናችን መሰረት የሆነ ጥልቅ ስነ-ልቦናዊ ትስስር ያለው የውሃ ላይ ፊደላችን ነው።

የሁላችንም የልብ ትርታ፣ የየቤታችን እና የጓዳችን የዘወትር ወግ፣ የውስጥ እንጉርጉሮአችን፣ እንዲሁም የዚህ ነቅቶ የተነሳ ትውልድ የጠዋትና የማታ፣ የማይነጥፍ የጋራ ቋንቋው የሆነው ለዚሁ ነው። አዛውንቱ በምርቃቱ፣ ወጣቱ በራዕዩ፣ እናት በማህጸኗ ፍሬ የምታስበው የሁላችንም የጋራ ቋንቋ ነው።

ቀይ ባህርን ስናነሳ እና ወደ እኛነቱ እንዲመለስ ስንጠይቅ፣ የሌላውን ሰው ሀብት የመቀማት ወይም የሌላውን ሉዓላዊነት የመንጠቅ ጉዳይ አድርገን አይደለም። ቀይ ባህር እጅግ ግዙፍ፣ ጥልቅ እና ሰፊ ነው፤ ለሁላችንም፣ ለጎረቤት ሀገራትም ተትረፍርፎ የሚበቃ፣ ሞልቶ የተረፈ ጸጋ አለው። የባህር በር ጥያቄያችን ጎረቤትን የመነቅነቅ፣ የማወክ ወይም ቀጣናዊ ሰላም የማደፍረስ ጉዳይ ፈጽሞ አይደለም። ይልቁንም ቀይ ባህር የተረጋጋ የሰላም፣ ጠንካራ የአብሮነት፣ የጋራ ብልጽግና እና የጠለቀ የመከባበር ጉዳይ ነው። ይህ የተፈጥሮ ጸጋ ከኢትዮጵያ ስነ-ልቦና፣ አፈ-ጣጠር እና ታሪካዊ እርሾ ጋር እጅጉኑ የተቆራኘ በመሆኑ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ አብሮ የማደግ ራዕይ ነው።

የባህር በር ጥያቄያችን ያንን በታሪክ የተፈጸመብንን ኢ-ፍትሃዊነት፣ ያንን አድሏዊነት፣ እና ያንን የታሪክ ሴራና ሻጥር ገርስሶ የመሰባበር ጉዳይ ነው። ይህ የዘመናት የታሪክ ስብራታችንን የመጠገን፣ ያረጀውን ቁስላችንን የማከም፣ እና የኢትዮጵያን ከፍታ እንደገና የማረጋገጥ ጥያቄ ነው። ይህንን የዘመን ስብራት ለመጠገን ደግሞ፣ ዛሬ ላይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከመቼውም ጊዜ በላይ ታሪካዊ አደራውን እና ሀላፊነቱን ለመወጣት በተጠንቀቅ ቆሟል። 

በቀይ ባህር ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ልቡ ቀጥ ያለ፣ አቋሙም እንደ አለት የጸና ነው።

በቅርብ ታሪካችን ለ27 ዓመታት በነበረው ስርአት፣ ስለ ቀይ ባህር ማውራት እንደ ትልቅ ወንጀል ተቆጥሮ በታፈንንበት ዘመን እንኳን፣ ህዝቡ ቀይ ባህርን ከልቡ ሰሌዳ አላጠፋውም።

"የውሻውን ነገር ለውሻው ተዉት" ተብሎ፣ ያንን ታሪካዊ ክብር እንድንረሳ፣ ያንን ባለቤትነት እንድንክድ በተገደድንበት በዚያ የጨለማ ዘመን እንኳን፣ ህዝቡ በየቤቱ እና በየጓዳው በሹክሹክታ እየመከረበት፣ የሆዱን በሆዱ ይዞ እያስታመመ የኖረበት ጥልቅ የማንነት ጉዳይ ነው።

ይህንን እውነት በድፍረት አደባባይ አውጥተው በመጠየቃቸው ብቻ በርካቶች ለእስር፣ ለስቃይ እና ለስደት ተዳርገዋል። ይህ የሚያሳየው ቀይ ባህር ለኢትዮጵያዊያን ከፖለቲካዊ ትርፍ የዘለለ፣ የመኖር እና ያለመኖር፣ የክብር እና የማንነት ጉዳይ መሆኑን ነው።

ተጨባጩ እውነት ይህ ሆኖ ሳለ፣ ኢትዮጵያን እና ቀይ ባህርን አርቆ፣ ነጥሎ እና አራርቆ ማቆየት በተፈጥሮም ሆነ በታሪክ ሚዛን ፈጽሞ የማይቻል ነው። ይህ አሁን ያለው ንቁ ትውልድ ይህንን ታሪካዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት ሙሉ በሙሉ ተዘጋጅቷል፤ ለዚህም ብቁ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል። በርካታ መሰናክሎችን ጥሶ ያለፈ፣ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ታላላቅ ትውልዳዊ ተልዕኮዎችን እውን ያደረገ፣ የማይበገር አሸናፊ ትውልድ ነው። በመሆኑም፣ ይህ ትውልድ በቀይ ባህር ላይ የተጠነሰሰውን የታሪክ ሻጥር በመስበር፣ ባህሩን ወደ ባለቤቱ፣ ወደ ርስቱ እና ወደ ተፈጥሯዊ ማንነቱ እንደሚመልሰው አንዳችም ጥርጥር የለውም።

አዎ! ይህ ትውልድ ለዚህ ታላቅ ተልዕኮ የተሟላ የትኛውም ዓይነት ዝግጁነት አለው። ከዳር እስከ ዳር፣ የሁላችንንም ልብ በአንድ ምት የሚያዘልለው፣ የነገ ተስፋችንን የሚያለመልመው አዲሱ መዝሙራችን እና የጋራ ቋንቋችን ቀይ ባህር ነው።

ታሪካዊ ክብራችን የሚመለሰው፣ የዘመናት ስብራታችን የሚጠገነው፣ ኢትዮጵያዊ ከፍታችን በተግባር የሚረጋገጠው ይህ የጋራ ቋንቋችን ወደ ቀድሞ ርስቱ ሲመለስ ነው። ቀይ ባህር የትናንት ታሪካችን፣ የዛሬው ህልውናችን፣ እና ብሩህ የነገያችን የማይነጥፍ ቋንቋችን ሆኖ በክብር ይቀጥላል! የትውልዱ ታላቅ አደራ ከግቡ ይደርሳል!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ