የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት በድንበሯ ምሰሶዎች እና በጦር ኃይሏ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በህዝቦቿ ልብ ውስጥ በሚታነጸው የጋራ መግባባት እና በማይናወጠው የአንድነት ዐለት ላይ የቆመ ነው።
ታላቂቱ ኢትዮጵያ፣ የዘመናት ፈተናዎችን ተሻግራ፣ የታሪክ አውሎ ንፋስ ውስጥ አልፋ ዛሬ ላይ የደረሰችው፣ በልጆቿ ደም እና አጥንት በተገነባ መስዋዕትነት ብቻ ሳይሆን፣ ከልዩነት ማዕበል በላይ በገነነ የውስጥ መተባበር እና የህብረት ጸጋ ነው።
ነገር ግን፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች፣ ይህች ሀገር ቀና ብላ እንዳትራመድ፣ የጋራ ቋንቋ እና አንድ የልብ ትርታ እንዳይኖራት የባቢሎንን የመከፋፈል እርግማን ሲያዘንቡባት ኖረዋል። አንድ ሆነን የብልጽግናን ግንብ እንዳንገነባ፣ ቋንቋችንን በማዘበራረቅ፣ አንዱን ወገን በመደለልና ሌላውን በማግለል፣ የልዩነትን እና የጥላቻን መርዝ ከጥንት ጀምሮ ሲግቱን ቆይተዋል።
የጠላቶቻችን ሴራ ጊዜና መልኩን ይቀይራል እንጂ አላማው አንድ እና ጥርት ያለ ነው፤ እርሱም ኢትዮጵያን የርስ በርስ ጦርነት አውድማ ማድረግ። ኢትዮጵያን ከሁለቱ ውኃዎቿ ማራቅ ነው፡፡ ወንድም በወንድሙ ላይ ጠመንጃ እንዲያነሳ፣ እልህ አስጨራሽ እና ትውልድ አምካኝ የእርስ በርስ መተላለቅ ውስጥ እንድንዘፈቅ ያልሸረቡት አሻጥር፣ ያልቆፈሩት የጥፋት ጉድጓድ አልነበረም።
አንዱን ወገን በስውር በማስታጠቅ ሌላውን በማዳከም፣ ለዘመናት በወንድማማቾች ደም ሲነግዱ ኖረዋል። ከዚህም አልፎ፣ የኢትዮጵያን ጂኦፖለቲካዊ ጡንቻ በማዛል፣ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ የባሕር በሯን በማሳጣት፣ የውኃ ላይ እትብቷን በመበጠስ፣ በየብስ እንድትታጠር አድርገዋል። በኢኮኖሚ ደቃ፣ በፖለቲካ ተከፋፍላ፣ እንደ ምስጥ በውስጧ በምትበላ ሀገር ላይ የራሳቸውን የባንዳ ዙፋን ለመትከል ያልፈነቀሉት ቋጥኝ አልነበረም።
ሆኖም፣ የኢትዮጵያ የእምቢተኝነት የአልደፈርባይነት መንፈስ በመከራ ውስጥ የሚጠነክር፣ በእሳት ውስጥ የሚፈተን ወርቅ ነው! ጠላቶቻችን "ተበታተኑ፣ ፈረሱ፣ አከተመላቸው" ሲሉን፣ እኛ ግን ከውድቀታችን አፈር ውስጥ ዳግም እንመዘዛለን። እነሆ፣ የፊታችን ሐምሌ 8 የሚጀመረው ታሪካዊው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፣ የፖለቲካ ስብራታችንን የምንጠግንበት፣ የዘመናት ቁስላችንን በይቅርታ የምናክምበት የህልውና እና የሉዓላዊነታችን ዋነኛ ምሰሶ ነው።
ይህ ጉባኤ፣ ተራ የፖለቲካ ልሂቃን የቃላት ጦርነት የሚደረግበት አውድማ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያን በአንድ ጣሪያ ስር ተሰባስበው፣ በገዛ ሀገራቸው ዕጣ ፈንታ ላይ የራሳቸውን የስምምነት ማህተም የሚያኖሩበት የነጻነት መድረክ ነው። ይህ የሰለጠነ መመካከር፣ በራሱ የሉዓላዊነት ከፍተኛ መገለጫ ነው፤ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትን በጽኑ የሚዘጋ፣ የጠላትን ሴራ ከስሩ የሚነቅል የብሔራዊ መግባባት የጋራ ቃል ኪዳን ነው።
ታሪክ እንደመሰከረው፣ ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ ሲመክሩ እና ሲተባበሩ የውጭ ጠላቶች በሃፍረት ይሸፈናሉ። ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን ትተን፣ "እኔ" ከሚለው ራስ ወዳድነት ወጥተን "እኛ" በሚል ጽኑ መንፈስ በአንድነት ስንቆም፣ የማይደፈረውን የዓባይን ወንዝ ገድበን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ እውን አድርገናል።
በተመሳሳይ፣ የዘመናት የውኃ ላይ እስራታችንን ለመበጠስ፣ ታሪካዊውን የባሕር በር እና የወደብ ባለቤትነት መብታችንን ለማረጋገጥ በምናደርገው ፍትሃዊ የዲፕሎማሲ እና የጂኦፖለቲካ ጉዞ፣ ዳግም ብሔራዊ አንድነታችንን ለዓለም እያረጋገጥን ነው። ጠላት ቋንቋችንን እንደ ባቢሎን ህዝብ ሊያከፋፍል ሲጥር፣ እኛ ግን የልማት፣ የሰላም እና የብልጽግናን አንድ ቋንቋ መናገር ጀምረናል።
በመሆኑም፣ ሐምሌ 8 የሚጠነሰሰው ሀገራዊ ምክክር፣ ኢትዮጵያን ከውስጥ አጽንቶ፣ ከውጭ የሚመጣባትን የጥፋት ማዕበል የሚመክት የማይበገር ጋሻችን ነው። በምክክሩ፣ ለዘመናት የተነዛው የጥላቻ እና የመከፋፈል ትርክት ይከሽፋል፤ በምክክሩ፣ ሀገረ-መንግሥቱን ለማፍረስ የተወጠነው የጠላት ሴራ የሸረሪት ድር ሆኖ ይበጠሳል! ዛሬ፣ ከስሜት ፖለቲካ ወጥተን፣ በምክንያት እና በስክነት ስንመክር፣ የዘመናት የኢትዮጵያ ጠላቶች አንገታቸውን ይደፋሉ።
የኢትዮጵያ ሕዳሴ፣ በልጆቿ የጠረጴዛ ዙሪያ ምክክር፣ በጥልቅ መከባበር እና በጽኑ አንድነት በአለት ላይ ተመስርቶ ወደ ፊት ይገሰግሳል። አዎ! በምክክሩ የጠላት ሴራ ይከሽፋል፤ ታላቂቱ ኢትዮጵያም ለዘላለም በክብር ጸንታ ትኖራለች!
በአዶኒያስ ወ/አረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: