የደኅንነት ትብብርን እና የፓርላሜንታዊ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚመክረው ዓለም አቀፍ የፓርላማ የመረጃና ደኅንነት ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በፎረሙ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ጉባኤው በሀገራት መካከል ስልታዊ አጋርነትንና ትስስርን በመፍጠር፣ ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ ሥጋቶችን በጋራ ለመሻገር ሰፊ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
መድረኩ ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የተንጸባረቀበትን 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ባካሄደችበት ማግሥት መደረጉ ልዩ ትርጉም እንዳለውም አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትን፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና መሰል የደኅንነት ሥጋቶችን ለመከላከል ከጎረቤት ሀገራት ጋር በቆራጥነትና በትኩረት እየሠራች እንደምትገኝም አብራርተዋል።
ከዚህም ባለፈ ሀገራችን የጤና ሥጋቶችንና ወረርሽኞችን ለመከላከል እንዲሁም የምግብ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ጠቁመዋል።
በዓለማችን ላይ ዋነኛ ሥጋት እየሆነ የመጣውን የሳይበር ደኅንነት አደጋ ለመቆጣጠር የሚያግዙ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀትና ከተለዋዋጭ የቴክኖሎጂ ዕድገቶች ጋር ራስን በማላመድ ረገድ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለጉባኤው ተሳታፊዎች አስገንዝበዋል።
ይህ ፎረም በዓለም ላይ ሥጋት የሆኑ ጉዳዮችን በዘላቂነት ለመፍታት በፓርላሜንታሪያን፣ በፖሊሲ አውጪዎች፣ በምሁራን እና በአጋር አካላት መካከል ልምድ ለመለዋወጥና ጽኑ አጋርነት ለመፍጠር እንደሚያግዝ መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።
በዚሁ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወከሉ የምክር ቤት አባላት፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የደኅንነት ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: