Search

እነሆ ዛሬም ሌላ አዲስ የላቀ የህክምና ማዕከል ተመርቋል፦ ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ዓርብ ሐምሌ 03, 2018 233

 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ውስጥ ዘመኑን የዋጀ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ እና የቅርብ ጊዜ ቴክኖሎጂዎችን ያሟላ ባለ 7 ወለል "የላቀ የህክምና ማዕከል" ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

ይህ ግዙፍ ማዕከል በነባሩ ሆስፒታል የነበረውን አቅም በእጥፍ የሚያሳድግ ነው።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማዕከሉ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ እንዳብራሩት፣ ነባሩ ሆስፒታል እጅግ ከማርጀቱ የተነሳ ለታካሚዎች መጨናነቅን የፈጠረ ከመሆኑም በላይ፣ በውስጡ የነበሩት ኋላቀር የህክምና መሳሪያዎች ለታካሚዎችም ሆነ ለባለሙያዎች ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ምቹ አልነበረም።

አስተዳደሩ ይህንን አስከፊ ሁኔታ ታሪክ በማድረግ፣ እጅግ ንፁህ እና ውብ የሆነውን ይህንን አዲስ የላቀ ማዕከል ለህዝብ ማበርከት ችሏል።

አዲሱን ማዕከል ልዩ የሚያደርገው የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች በሙሉ የተሟሉለት መሆኑ ነው።

እንደ ከንቲባዋ ገለፃ፣ ማዕከሉ የ2026 ምርት የሆኑና የሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) የሚጠቀሙ ዲጂታል ኤምአርአይ (MRI)፣ ሲቲ ስካን፣ አልትራሳውንድ እና ተንቀሳቃሽ የኤክስሬይ ማሽኖች ተሟልተውለታል።

ከዚህም በተጨማሪ በሰዓት 30 ሺህ ሊትር ማምረት የሚችል የኦክሲጅን ማምረቻ የተተከለ ሲሆን፣ ቀድሞ የነበረው የአስተኝቶ ህክምና አልጋ ቁጥር ከ147 ወደ 360፣ የኦፕሬሽን ክፍሎች ከ3 ወደ 7 እንዲሁም የፅኑ ህክምና ክፍሎች ወደ 19 በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ ችለዋል።

ማዕከሉ ስታንዳርዱን የጠበቀ ሰፊ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎትን፣ የሰራተኛ ማረፊያ ክፍሎችን፣ ቤተ-መጻሕፍትን፣ ዘመናዊ ቢሮዎችን፣ መሰብሰቢያ አዳራሾችን እና የካፍቴሪያ አገልግሎቶችን ለታካሚዎችና ለባለሙያዎች በሚመች መልኩ አሟልቶ ይዟል።

በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የጤና አገልግሎት ፍላጐት በመንግስት ብቻ የማይሟላ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የግሉን ዘርፍ ጭምር በመደገፍ ዜጎች ከፍተኛ ወጪ አውጥተው ወደ ውጭ አገራት በመሄድ ያደርጉት የነበረውን ህክምና በአገር ውስጥ መስጠት እንዲቻል በስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

ይህ ዘመናዊ ማዕከልም ሀገራችን ዓለም በዘርፉ የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ የጀመረቻቸው ጠንካራ ሥራዎች ሕያው ምስክር መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህ ግዙፍ የላቀ የህክምና ማዕከል በፍጥነትና በጥራት ተገንብቶ አገልግሎቱን በእጥፍ በማሳደግ ለህዝብ እንዲበቃ ሌሊትና ቀን አብረው ለነበሩ፣ ለተባበሩ እና ግንባታውን ላከናወኑ አካላት በሙሉ በራሳቸውና በታካሚዎች ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: