Search

በውኃ እና ሳኒቴሽን ዘርፍ አፍሪካ አበረታች እምርታ አስመዝግባለች፦ ተመድ

ዓርብ ሐምሌ 03, 2018 160

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2026 የዘላቂ ልማት ግብ 6 (SDG 6) አጠቃላይ ሪፖርት አፍሪካ በውኃ እና ሳኒቴሽን ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን አዎንታዊ ለውጥ ይፋ አድርጓል።

ከድንበር ተሻጋሪ የውኃ ትብብር አኳያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል። በአውሮፓውያኑ 2020 ከነበሩት አምስት ሀገራት በመነሳት፣ በ2023 16 ሀገራት 90 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆነውን የድንበር ተሻጋሪ ተፋሰስ የውኃ ትብብር ስምምነቶችን ተግባራዊ ማድረግ ችለዋል።

ለዚህም እንደ ጥሩ ማሳያ የሚነሳው በጋምቢያ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ሞሪታኒያ እና ሴኔጋል መካከል የተደረገው የሴኔጋሎ-ሞሪታኒያ የከርሰ ምድር ውኃ ስኬታማ የትብብር ማዕቀፍ ነው።

ይህም የከርሰ ምድር ውኃን በፍትሃዊ እና ዘላቂነት ባለው መልኩ ለማስተዳደር ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በዚህም ሦስቱ ሀገራት የትብብር ውጤታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻል የቻሉ ሲሆን፣ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የድንበር ተሻጋሪ ተፋሰስ ክፍልም በስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል።

በሌላ በኩል በሰሜን አፍሪካ ክልል ከ2020 ወዲህ የውኃ አጠቃቀም ቅልጥፍና በ12 በመቶ ማደግ መቻሉ በሪፖርቱ ተገልጿል።

ይህ ከ2020 በኋላ የታየው እድገት የተጠናከረ የፖሊሲ ትኩረትን እና በዘርፎች መካከል የተሻለ የውኃ ክፍፍል መኖሩን የሚያመላክት ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት አስተማማኝ የመጠጥ ውኃ አገልግሎቶችን በሚመለከት መረጃን የማሰባሰብ አቅም ከ2017 ጀምሮ በአራት እጥፍ ያደገ ሲሆን ይህም የዘላቂ ልማት ግቡን ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት አፋጥኖታል።

የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድም አበረታች ጅምሮች አሉ። ወደ 80 በመቶ የሚጠጉት ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የሴቶችን የውኃ አስተዳደር ተሳትፎ በሕግ እና በፖሊሲ ማዕቀፎቻቸው ውስጥ በግልጽ ማካተት ችለዋል።

በፈጠራ እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የዜጎችን ሳይንሳዊ መረጃ በብሔራዊ የክትትል ሥርዓት ውስጥ በማካተት በስድስት የአፍሪካ አገራት በመተግበር ላይ ይገኛል።

የአፍሪካ ኅብረት የ2026 ዓመትን የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት "ዘላቂ የውኃ አቅርቦት እና ደህንነቱ የተጠበቀ የሳኒቴሽን ሥርዓትን የማረጋገጫ ዓመት" አድርጎ የሰየመ ሲሆን፣ የአፍሪካ መሪዎችም የ"አፍሪካ የውኃ ራዕይ 2063"ን በይፋ በማስጀመር የውኃ እና ሳኒቴሽን ጉዳይን የአህጉሪቱ የልማት እና የፖለቲካ አጀንዳ ማዕከል አድርገውታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: