Search

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውስብስብ አሰራሮችን በማቃለል ጊዜና ገንዘባችንን ታድጎልናል፡- የኢሉአባቦር ዞን ነዋሪዎች

ዓርብ ሐምሌ 03, 2018 112

 

በኢሉአባቦር ዞን ያዮ ወረዳ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው "መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን አዝጋሚና አሰልቺ የመንግሥት ተቋማት የአሠራር ሂደት በማዘመን እንግልትንና አላስፈላጊ ወጪን ማስቀረቱን የዞኑ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከል አገልግሎት ፍለጋ ሲባክን የነበረውን ጊዜና ገንዘብ ማዕከሉ በከፍተኛ ደረጃ እንደታደጋቸው በመጥቀስ፣ ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ስፍራ ማግኘት መቻላቸው ውስብስብ ውጣ ውረዶችን እንዳቃለላቸውና ታላቅ እፎይታ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።

የያዮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በፍቃዱ ኦልጅራ በበኩላቸው፣ ማዕከሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ በማዘመን ማኅበረሰቡ ፈጣን፣ ቀልጣፋና የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኝ ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሠረተ ልማት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ማዕከሉን መርቀው ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ "መሶብ" የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተበታተነ መልኩ ይሰጡ የነበሩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ሥር በማሰባሰብ ለተገልጋዩ ማኅበረሰብ በጥራትና በተደራሽነት ለማቅረብ የተዘረጋ ሥርዓት መሆኑን አብራርተዋል።

አያይዘውም ማዕከሉ ብልሹና ኋላቀር አሠራሮችን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ በማስቀረት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የተቀናጀ የዲጂታል አሠራርን የሚከተል በመሆኑ አላስፈላጊ ወጪዎችን ከመቆጠብ ባለፈ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስገንዝበዋል።

በሚፍታህ አብዱልቃድር

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: