ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ ውስብስብ የፖለቲካ እና የማህበራዊ አለመግባባቶቿን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የምታደርገው ታሪካዊ ጥረት አሁን ላይ ወደ ወሳኙ ምዕራፍ ተሻግሯል።
ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን (ከየካቲት 2014 እስከ 2018 ዓ.ም) ላለፉት አራት ዓመታት ያደረገው ጉዞ እጅግ ሰፊ፣ አሳታፊ እና ሁሉንም ያካተተ መሆኑን ከሂደቱ በስተጀርባ ያሉ አሃዞች በግልጽ ያሳያሉ።
ይህ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ጉዞ አሁን ላይ ፍሬ አፍርቶ መላው ኢትዮጵያዊ በጉጉት ወደሚጠብቀው ታሪካዊው ሀገራዊ ጉባኤ ተደርሷል።
ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያደርገው ጉዞ እጅግ ሰፊ እና አሳታፊ መሆኑን ከሂደቱ ጀርባ ያሉ አሃዞች በግልጽ ያሳያሉ።
የኮሚሽኑ ምስረታ ራሱ የሕዝብን ድምፅ መሠረት ያደረገ ነበር። በወቅቱ ከሕዝብ ጥቆማ የቀረቡ 632 ዕጩዎች የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውድድር 42 ዕጩዎች ቀርበዋል። በመጨረሻም ይህንን ታሪካዊ የሀገራዊ ምክክር ሂደት በብቃት እንዲመሩ 11 ኮሚሽነሮች ተመርጠው ወደ ሥራ መግባታቸው ይታወሳል።
ኮሚሽኑ ወደ ዋናው ሥራ ከመግባቱ በፊት የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎችን በስፋት አከናውኗል። በዚህም በሁለት ዙሮች የቅድመ-ምክክር እና የምክክር ሥነ-ዘዴ ማስተዋወቂያ ሕዝባዊ ውይይቶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በማካሄድ ጠንካራ መሠረት ጥሏል። የኮሚሽኑ ሀገራዊ ተደራሽነትም ቢሆን እጅግ አስደናቂ የሚባል ነው።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ በየወረዳው የሚገኙ አስር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ማህበራዊ መሰረቶችን ያሳተፈ ሲሆን፣ ይህ ሂደት በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ አንድ ሺህ 195 ወረዳዎች ውስጥ ተፈጻሚ ሆኗል። ለዚህ ግዙፍ ስራ ስኬትም አስራ አምስት የክልል ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች በህዝብ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተቋቁመው አገልግሎት ሰጥተዋል።
በዚህ ሰፊ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሰባት የተለያዩ የተባባሪ ተቋማት ተሳትፈዋል። ከየወረዳውና ከየሕብረተሰብ ክፍሉ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ወኪሎችን በማስመረጡ ተግባር ላይ ኮሚሽኑን ያገዙ ስምንት ሺህ 515 ተባባሪ አካላት (ግለሰቦችና ባለሙያዎች) የነበራቸው ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም። ይህ ሁሉ ጥረት የምክክር ሂደቱ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ድምጽ ያካተተ እንዲሆን ያለመ መሆኑን ያሳያል።
የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያቀፈ ነው። ሃያ አንድ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላት፣ ሰላሳ ስምንት የፌዴራል ባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም ስምንት የዲያስፖራው ባለድርሻ አካላት በሂደቱ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ ተደርጓል። ይህ ስብጥር የምክክር ሂደቱን ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ምልከታን ያካተተ፣ እንዲሁም ሁሉንም አሳታፊ ያደርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አሁን ላይ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከቅድመ ዝግጅት፣ ከተሳታፊዎች ልየታ ፣ ከወኪሎች ምርጫ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ተሻግሮ ወደ ዋናው የምክክር ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡
ኮሚሽኑ ለዋናው የምክክር ጉባኤ ላይ የሚወያይባቸውን ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን በቅርቡ ለህዝቡ ያሳወቀ ሲሆን በፊታችን ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዋናው የምክክር ጉባኤ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
በዚሁ ትልቅ ተስፋ በተጣለበት እና ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሄ ሀሳቦች በሚቀርቡበት ትልቄ ጉባኤ ላይ ለማሳተፍ ቀድመው የተለዩ ተሳታፊዎች አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛል፡፡
አጠቃላይ ይህ ከምስረታ እስከ አጀንዳ አሰባሰብ የተጓዘው የቁጥሮች እና የሥራዎች ጉዞ የሚያመላክተው፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ከዳር እስከ ዳር የሕዝብን ድምፅ ሰምቶ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በፅኑ መሠረት ላይ የቆመ መሆኑን ነው።
ከሐምሌ 8 ጀምሮ የሚካሄደው ታላቁ ጉባኤ የዓመታት ድካም ፍሬ የሚታይበት፣ ልዩነቶቻችንን በውይይት ፈትተን አዲስ የምክክር ባህል የምንገነባበት የታሪክ ምዕራፍ ነው። የኢትዮጵያን ብሩህ ነገ ዛሬ ላይ በጋራ ውይይት እንገነባለን! ጉባኤው ለሀገራችን ሰላምና አንድነት ስኬታማ እንዲሆን እንመኛለን!
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: