Search

ምድርን ከአረንጓዴ ልባስ፣ አርሶ አደሩን ከገቢ ምንጭ ጋር ያገናኘው አረንጓዴ ዐሻራ

ዓርብ ሐምሌ 03, 2018 125

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ምድርን በአረንጓዴ ተክሎች ከመሸፈንና የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ፣ ሀገራዊ የምግብ ዋስትናንና ምርታማነትን ወደማረጋገጥ የተሸጋገረ ታላቅ ስኬት እየመዘገበ ይገኛል።

ቀደም ሲል ለደን ጥበቃና ለተራቆቱ መሬቶች ማገገሚያ ብቻ ትኩረት ይሰጥ የነበረው ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ፣ አሁን ላይ ስትራቴጂካዊ ለውጥ በማድረግ የአካባቢ ጥበቃን ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጋር ያቀናጀ የኢኮኖሚ ምሶሶ ለመሆን በቅቷል።


ይህ ስኬት በጉልህ ከሚታይባቸውና ትልቅ እመርታ ከተመዘገበባቸው ዘርፎች መካከል የፍራፍሬ ምርት ልማት ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተሻሻሉና ፍሬያማ የሆኑ የአቮካዶ፣ የማንጎ፣ የፓፓያ እና የኮምጣጤ ፍራፍሬዎች ዝርያዎች በስፋት እንዲተከሉ መደረጉ በየደረጃው ለሚገኙ አርሶ አደሮችና አምራቾች አዲስ የገቢ ምንጭ ፈጥሯል።

ንቅናቄው የአፈር መሸርሸርን በዘላቂነት ከመግታት ባለፈ፣ የመሬትን ለምነት በማሻሻልና የከርሰ-ምድር ውኃን በመጠበቅ ለፍራፍሬ ልማትና ለተሻሻለ ግብርና እጅግ ምቹ የሆነ ሥነ-ምህዳራዊ ሁኔታን ፈጥሯል።

ይህ የምርታማነት እመርታ አርሶ አደሩን ከራስ-አልፎ ለገበያ እንዲያመርት ከማስቻሉም በላይ፣ በከተሞች የሚስተዋለውን የፍራፍሬ አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት እያቃለለ ይገኛል።

ከዚህም ባሻገር፣ ጥራቱን የጠበቀ የፍራፍሬ ምርት በስፋት መመረቱ የኢትዮጵያን የኤክስፖርት አቅም በማሳደግና ወደ ውጭ የመላክ ዕድሎችን በማስፋት የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት የራሱን የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ተፈጥሮን ከመንከባከብና ምድርን ከማልበስ ባለፈ፣ የዜጎችን ማዕድ በሥርዓተ-ምግብ እራስን ወደመቻል ያሸጋገረ ፕሮጀክት ነው። የአካባቢ ጥበቃና የኢኮኖሚ ዕድገት እንዴት እጅና ጓንት ሆነው እንደሚጓዙ እና የአየር ንብረት መከላከል ወደ ተጨባጭ ምርታማነት እንዴት እንደሚቀየር ያሳየ ሕያው ሀገራዊ ማረጋገጫ ሆኗል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: