Search

በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ኢትዮጵያ አበረታች ሥራዎችን እያከናወነች ነው፡- ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)

ዓርብ ሐምሌ 03, 2018 171

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የፓርላማ የመረጃና ደኅንነት ፎረም ላይ፣ ኢትዮጵያ ደኅንነቱ የተጠበቀ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት እየሠራች መሆኑን የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ገለጹ።

ዋና ዳይሬክተሩ ለፎረሙ ተሳታፊዎች በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት ለማስፋትና ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችሉ በርካታ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ እንደምትገኝ አስታውቀዋል።

በተለይም ቴክኖሎጂውን ለቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት፣ ለሰላም ግንባታ ሂደትና ለመንግሥታዊ አገልግሎቶች ቅልጥፍና በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

ዘርፉ የሚያስከትላቸውን ወቅታዊ የደኅንነት ሥጋቶች ለመቀነስና አጠቃቀሙን በሕጋዊ ማዕቀፍ ለመምራት የሚያስችሉ ዘመናዊ የሕግ ዝግጅቶች በስፋት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ዓለም አቀፋዊ ፎረም ላይ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ዙሪያ ባሉ ወቅታዊ የደኅንነት ሥጋቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች እየቀረቡበትና ሰፊ ውይይት እየተደረገባቸው እንደሚገኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: