ለዘመናት የሀሳብ ልዩነትን ስንፀየፍ፣ ከእኛ የተለየ እይታ እና ሀሳብ ያለውን ወንድማችንን እንደ ባዕድ ጠላት ስንቆጥር፣ ስናሳድድ እና ስንወጋ ኖረናል።
መጋጨትን እንደ ጀግንነት፣ መቋሰልን እንደ ጀብዱ፣ በገዛ ወንድም ላይ ጦር መምዘዝን ደግሞ እንደ ባህል ቆጥረን በርካታ ዘመናትን በከንቱ አሳልፈናል።
የኃይል እርምጃን እና ግጭትን የችግሮቻችን መፍቻ ብቸኛ ቁልፍ አድርገን በመውሰድ በርስ በርስ ጦርነት እቶን ውስጥ እጅግ ብዙ ዋጋ ከፍለናል።
ነገር ግን ዛሬ ላይ ቆም ብለን የህሊና ሚዛን እናንሳ፤ ከዚህ ሁሉ መገዳደል እና መገፋፋት ምን አተረፍን?
ቆም ብለን በጥልቀት ስናስበው መልሱ እጅግ መሪር እና ልብ ሰባሪ ነው፤ "አንዳችም ያተረፍነው ነገር የለም" የሚል፡፡
ያተረፍነው ቢኖር ሀገር ሊገነባ፣ ታሪክ ሊቀይር እና ተዓምር ሊሠራ የሚችልን አምራች ትውልድ ማጥፋት፣ ማሳደድ እና እምቅ አቅሙን ማምከን ብቻ ነው።
በተለይም ሀገራችን ኢትዮጵያችን ከዚህ የጥፋት አዙሪት ያገኘችው ትርፍ ቢኖር የልጆቿን መራራ ሞት፣ የእናቶችን እሪታ፣ ከዓለም ወደኋላ የቀረ ዕድገትና ጭራ መሆን፣ የደቀቀ ኢኮኖሚን ብቻ ነው። ከመዋጋት ያተረፍነው ኪሳራን ብቻ ነው ማለት ይኸ ነው፡፡
የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ እስካለ ድረስ የሀሳብ ልዩነት መኖሩ የማይካድ የተፈጥሮ ሕግ ነው።
ዛሬም ልዩነቶች አሉን፣ ወደፊትም የተለያየ ሀሳብ ይኖረናል፤ መለያየት ዛሬ የተፈጠረ አዲስ ክስተት አይደለም፤ በየትኛውም የዓለም ጥግ ያለ የተፈጥሮ ሕግ ነው።
ሁላችንም ለሀገራችን የሚጠቅም የራሳችን የሆነ የመፍትሔ መንገድ፣ የራሳችን የሆነ እይታ ሊኖረን ይችላል።
ነገር ግን ይህ የሀሳብ ልዩነት ሊያጠፋፋን፣ ሊያፋጀን እና ሀገር ሊያፈርስ አይገባም። ለልዩነቶቻችን አደብ እና የሰለጠነ ገደብ ልናበጅላቸው ግድ ይላል።
ከልዩነት ጋር አብሮ ለመኖር እና ብልጽግናን ለማምጣት ብቸኛው መንገድ መወያየት ነው። አዎ! መወያየት የሰለጠነ ማኅበረሰብ መንገድ ነው! በመወያየት እና በውይይት የማይፈታ የተቆለፈ ችግር፣ በመመካከር የማንሻገረው ጎባጣ መንገድ በዚህች ምድር ላይ የለም።
ጠመንጃ የጥፋት እና የሞት እንጂ የመፍትሔ እና የሕይወት ቋንቋ ሆኖ አያውቅም። ለዚህ ደግሞ ከእኛ በላይ ምስክር ከየትም አይመጣምለለ
ስለዚህ ከመዋጋት ሺህ ጊዜ እንወያይ፤ ከመገዳደል ሺህ ጊዜ እንመካከር፤ ከመገፋፋት ሺህ ጊዜ ሀሳባችንን ጠረጴዛ ላይ አንስተን እንጣል!
የሀሳብ ልዩነታችን የጥፋታችን ምክንያት እንዳይሆን፣ ክብ ጠረጴዛ እና የሰለጠነ የውይይት መድረክ እስካለ ድረስ፣ የፈለግነውን የልዩነት ሀሳብ ከጠመንጃ አፈሙዝ እና ከጥይት ባሻገር ወደ ጠረጴዛ እናምጣ።
የጦርነትን አክሳሪነት ተረድተን፣ የሰላምን ውድ ዋጋ አውቀን፣ ከመዋጋት ይልቅ መመካከርን ቋሚ ባህላችን እናድርግ።
ታላቂቱ ሀገር የምትገነባው በጠመንጃ ኃይል እና በጉልበት ሳይሆን፣ በሀሳብ ልዕልና፣ በምክክር አውድማ እና በሰለጠነ የውይይት ባህል ነው፡፡
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: