የመደመር መንግሥት የሀገረ መንግሥት ግንባታን ካለፉት አዎንታዊ ስኬቶች በመነሳት፣ ስህተቶችን በማረምና አዳዲስ አሠራሮችን በመዘርጋት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የተቀረጸ መሪ እሳቤ ነው።
ይህ እሳቤ በፖሊሲና በስትራቴጂ ደረጃ ወደ ተግባር ሲቀየር ዋና ትኩረቱን ያደረገው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ማምጣት፣ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ማፋጠን፣ የሰው ኃይልን ማልማት እና ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ነው።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የዚህ እሳቤ ዋነኛ ማሳያዎች ሲሆኑ፣ ሀገራችን በራሷ አቅምና ብልሃት ወደፊት እንድትራመድ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ጥለዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የታዩት ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች የተከናወኑበት ፍጥነት እና የጥራት ደረጃ ቀደም ሲል ከነበረው የተለመደ የዘገየ አሠራር ፍጹም የተለየ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው።
የአዲስ አበባ እና የክልል ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምዕራፎች፣ የኢንጦጦ ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲሁም በየክልሎቹ የተገነቡት ዘመናዊ የኮንፈረንስ ሪዞርቶች እና የቱሪስት መዳረሻዎች የዚህ አዲስ አፈጻጸም ማሳያዎች ናቸው።
እነዚህ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው አጭር ጊዜ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ጥራት መጠናቀቃቸው፣ ሀገራችን ትላልቅ እቅዶችን በአጭር ጊዜ የመፈጸም አቅም እንዳላት በተግባር ያሳየ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ታከናውናለች የሚለውን መርህም እውን አድርጎታል።
የመደመር መንግሥት እነዚህን የልማት ሥራዎች ያከናወነው እጅግ ፈታኝ በሆኑ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ውስጥ አልፎ ነው።
ኢትዮጵያ ከውስጥ ሰላም መታወክ እና ከዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫናዎች ጋር እየታገለችም ቢሆን፣ የጀመረቻቸውን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ለአፍታም አላቆመችም። በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥም ሆና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ስኬታማ ሆናለች።
እንዲሁም በቴክኖሎጂው ዘርፍ የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ስልጠና እና የተቀናጁ የዲጂታል አገልግሎቶች እንደ መሶብ መተግበሪያ ይፋ ሆነዋል፣ በንግዱ ዘርፍም የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር እና የብሪክስ ትብብር ሥራዎች ስኬታማነቷን እያሳዩ ይገኛሉ።
ይህም የሚያሳየው ፈተናዎች የኢትዮጵያን ጉዞ እንደማያስተጓጉሉና ይልቁን አዳዲስ የጽናትና የስኬት ታሪኮችን ለመጻፍ ዕድል መሆናቸውን ነው።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: