Search

ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የሚወስዳት ብቸኛው መንገድ

ቅዳሜ ሐምሌ 04, 2018 61

 የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላለፉት አያሌ ዓመታት የታሪክ ጠባሳዎችን፣ የጽንፍ ርዕዮተ-ዓለማትን እና "እኔ ካልመራሁ እንጠፋፋለን" የሚሉ አጥፊ ትርክቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል።

ይህ አካሄድ ሀገራችንን ለከፋ የእርስ በርስ ግጭት፣ ለሕዝብ መፈናቀል እና ለከፍተኛ ማኅበራዊ ስብራት ዳርጓት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

ነገር ግን ከእነዚህ ሁሉ መከራዎች እና ውጣ ውረዶች በኋላ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምኅዳር ውስጥ አንድ አዲስና ተስፋ ሰጪ ጭላንጭል መታየት ጀምሯል።

ይህም ከመጠፋፋት ፖለቲካ ወደ መደማመጥ ባህል መሸጋገር ነው። የሀገራችንን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን እጅግ ወሳኝ ምዕራፍም ነው።

ለረጅም ጊዜ የዘለቀውና "የእኔ መንገድ ብቻ ነው ትክክል" የሚለው የፖለቲካ ጽንፈኝነት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያመጣው ትርፍ ቢኖር የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ብቻ ነው።

የፖለቲካ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍታት ይልቅ በኃይል እና በማግለል ለመፍታት የሞከሩባቸው ዓመታት ሀገራችንን ወደ ገደል አፋፍ አድርሷት ነበር። ይህ ውድቀት ግን ለአንድ ትልቅ እውነት በር ከፋች ሆኗል።

ይህም በጦርነትና በመጠፋፋት የሚያሸንፍ የለም፤ አሸናፊውም ተሸናፊውም አብረው ይከስራሉ የሚለው ነው።

ይህ ከመጠፋፋት ወደ መደማመጥ የመሸጋገር ሂደት በድንገት የተከሰተ ሳይሆን፣ በሕዝቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ እና በተለያዩ ተቋማዊ ጥረቶች የመጣ ነው።

በተለይም የሀገራዊ ምክክር መድረክ የተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ ስብስቦች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጡ ዕድል ይፈጥራል፡፡

በዚህም ታሪካዊ ቅሬታዎች እና የትርክት ልዩነቶች በጠብመንጃ ሳይሆን በሐሳብ እንዲሞገቱ በማድረግ፣ "እኔ ብቻ ልደመጥ" ከሚል አባዜ ወጥቶ "የሌላውንም ወገን ስጋት እና ፍላጎት ልረዳ" የሚል ብስለት ይመጣሉ።

መደማመጥ በሁሉም ነገር መስማማት ሳይሆን ልዩነቶችን በሰላማዊ፣ በሠለጠነ እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ መቻል ነው።

በዚህ የሽግግር ወቅት የይዘት ፈጣሪዎች፣ የሚዲያ ተቋማት እና የፖለቲካ ተንታኞች ሚናም ከጦርነት ነጋሪት ጎሳሚነት ወደ ሰላም አምባሳደርነት መቀየር አለበት።

ጥላቻንና መከፋፈልን የሚሰብኩ ትርክቶች በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነታቸው እየቀነሰ፣ ይልቁንም ምክንያታዊነት፣ መቻቻል እና የጋራ ጥቅምን የሚያስቀድሙ ይዘቶች ቦታ እያገኙ መጥተዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው "መደማመጥ" መንገድ የኅልውናዋ ዋስትና ነው። ፖለቲካዊ ኃይሎች የጋራ ማንነታችንን ሳያጠፉ ልዩነቶቻቸውን ውበት አድርገው መያዝ የሚችሉት ማዳመጥን ባህላቸው ሲያደርጉት ብቻ ነው።

ከመጠፋፋት አዙሪት ወጥተን እርስ በርስ ለመደማመጥ የጀመርነው ጉዞ፣ ወደ ዴሞክራሲያዊት እና የበለጸገች ኢትዮጵያ የሚያደርሰን ብቸኛው እና አስተማማኙ ድልድያችን ነው።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: