Search

የኢትዮጵያ ብቃት፡ ከራስ አልፎ ለቀጣናው የተዘረጋው የሰላም ክንድ

እሑድ ሐምሌ 05, 2018 28

የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ብሔራዊ ክብር በፅኑ መሠረት ላይ የሚቆመው፣ አካታች፣ ጠንካራ እና ዘመኑን በሚመጥን የፀጥታ ተቋም ሲታጀብ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ባደረገው እጅግ ጥልቅ እና ሁለንተናዊ የተቋም ሪፎርም፣ ከታሪካዊ ውጣ ውረዶች እና ስብራቶች ተሻግሮ በአዲስ መልክ ዳግም ተወልዷል።

ይህ ዳግም ልደት በሰራዊት ቁጥር ማደግ እና በትጥቅ መብዛት የሚገለፅ ሳይሆን፣ የላቀ የሥነ-ልቦና፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትጥቅ እና የስትራቴጂካዊ የአስተሳሰብ ልዕልናን በተጨባጭ ያረጋገጠ ታሪካዊ የለውጥ ሽግግር ነው።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ፣ "የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ስጋት ላይ የሚጥል ቅንጣት ታክል ስጋት የለም" ሲሉ በልበ ሙሉነት የገለፁት ሀሳብ፣ የዚህ ጥልቅ ሪፎርም ተጨባጭ ፍሬ እና ህያው ምስክር ነው።

ይህ አባባል በፖለቲካዊ መድረክ የሚሰነዘር  የቃላት ድርደራ ሳይሆን፣ መሬት ላይ ባለው እውነተኛ የመከላከል አቅም (Deterrence) እና በቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ ማረጋገጫ ነው።

ሠራዊቱ የውጭ ጥገኝነትን በቆራጥነት ሰብሮ የራሱን ዘመናዊ የድሮን ቴክኖሎጂዎች እና ወታደራዊ ቁሳቁሶች በኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት መጀመሩ፣ እንዲሁም ተለዋዋጭ የሆነውን ጂኦፖለቲካዊ አውድ የሚመጥን የላቀ አቅም መገንባቱ፣ ትንኮሳ ለማድረግ የሚዳዳውን የትኛውም ሀይል አስቀድሞ አስር ጊዜ እንዲያስብ እና እጁን እንዲሰበስብ የሚያስገድድ ነው።

"የኢትዮጵያ ብቃት ከራስ አልፎ ለቀጣናው" የሚለው እሳቤ፣ የኢትዮጵያን የዘመናት ጂኦፖለቲካዊ ሚና በሚገባ የሚያንፀባርቅ ነው። ጠንካራ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መገንባት ለኢትዮጵያውያን የህልውና እና የሰላም ዋስትና ከመሆን አልፎ፣ ለአፍሪካ ቀንድ እጅግ አስተማማኝ የፀጥታ ምሰሶ ነው።

ኢትዮጵያ በራሷ የቴክኖሎጂ አቅም ያደረጀችው ወታደራዊ ኃይል እና ዳግም ያቋቋመችው ዘመናዊ የባህር ኃይል፣ ቀጣናዊ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት፣ የንግድ እና ደህንነት ቀለበቶችን ለመጠበቅ እንዲሁም አህጉራዊ ሰላምን ለማስፈን የማይተካ ሚና አለው። ኢትዮጵያ ስትረጋጋ ቀጠናው በሰላም ይተነፍሳል፤ ኢትዮጵያ ስትገዝፍ ደግሞ ቀጠናው በዓለም አደባባይ ይከበራል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማረጋገጫ የሚያመላክተው ሌላው መሰረታዊ ቁምነገር፣ የሠራዊቱ ሪፎርም ከገዢ ስርዓት ጠባቂነት ወደ እውነተኛ የሀገርና የህዝብ ሉዓላዊነት ዘብነት ሙሉ በሙሉ መሸጋገሩን ነው።

ይህ አዲስ ሀገራዊ ቁመና፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር፣ ዜጎች በልበ ሙሉነት እና ያለስጋት ወደ ልማት ስራቸው እንዲያተኩሩ የሚያስችል ነው። "ቅንጣት ታክል ስጋት የለም" ሲባል፣ ጠላቶች ወይም ስጋቶች ጨርሶ አይፈጠሩም ማለት ሳይሆን፣ የሚመጡትን ማናቸውንም የደህንነት ስጋቶች በአስተማማኝ ሁኔታ ለመመከት የሚያስችል በፅኑ አለት ላይ የቆመ፣ ፈተናዎችን የተሻገረ የተሰናዳ ክንድ አለን ማለት ነው።

በአጠቃላይ ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ በጥልቅ ሪፎርም ያገኘው ታሪካዊ ዳግም ልደት፣ ብሔራዊ ክብራችንን በማይናወጥ መሰረት ላይ አፅንቷል። ይህ አቅም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የማዕዘን ድንጋይ ከመሆኑም በላይ፣ ቀጠናዊ ሰላምን የሚያፀና የጋራ አህጉራዊ ኩራት ሆኗል።

ኢትዮጵያን ከማፅናት አልፎ፣ የቀጣናውን የሰላም እና የልማት ትርክቶች በአዲስ መልክ በደማቁ እየፃፈ ይገኛል። የኢትዮጵያ የፀጥታ ብቃት፣ በእርግጥም ከራስ አልፎ ለቀጠናው የተዘረጋ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ጠንካራ የሰላም ክንድ ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ:

ተያያዥ ዜናዎች: