Search

የአውሮፕላን ማረፊያው ምርት እና ምርታማነትን እንድናሳድግ የሚያስችለን ነው፡- ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

እሑድ ሐምሌ 05, 2018 22

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለኃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፤ ዛሬ የተመረቀው የአውሮፕላን ማረፊያ ፋይዳው ብዙ ነው ብለዋል። የተጋመደች ኢትዮጵያን የበለጠ ለማስተሳሰር፣ ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እና ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አንስተዋል።

የአውሮፕላን ማረፊያው ምርት እና ምርታማነትን እንድናሳድግ የሚያስችል ነው ያሉትር ርዕሰ መሥተዳድሩ፤ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑንም አንስተዋል።

ደብረ ማርቆስ ከተማ የጎጃም ክፍለ ሀገር መቀመጫ ሆና ለረጅም ጊዜ ያገለገለች፣ ማዕከላዊ መንግሥቱን ከሰሜን ምዕራብ ጋር ስታገናኝ የኖረች ናት ብለዋል።

በውስጧ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ሃብቶችን ያቀፈች መሆኗንም ገልጸዋል። ከዓመታት በፊት የአየር መንገድ ተጠቃሚ የነበረች ቢሆንም በመካከል ተቋርጦ የሕዝብ ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል።

ደብረ ማርቆስ የበርካታ ጸጋዎች ባለቤት እንደሆነች ያነሱት አቶ አረጋ፤ የከተማዋ ሕዝብ የአውሮፕላን ማረፊያ ጥያቄን ለዓመታት ሲጠይቅ ቆይቷል፤ ነገር ግን አይሆንም የሚል ተስፋ አስቆራጭ መልስ ይሰጠው እንደነበር አንስተዋል።

አሁን ግን ያ ተስፋ ጥያቄ መልስ አግኝቶ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል። ሌሎች ጥያቄዎችም ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ ተስፋ አለኝ፤ ነገር ግን የልማት ሥራዎችን ለማረጋገጥ ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከዓመታት በፊት አይሆንም የተባለው ተስፋ አስቆራጭ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ላደረጉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በመጨረሻም  የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: