የመግባባት ዴሞክራሲ መሠረታዊ መርሕ የፖለቲካ ሥልጣንን በአሸናፊ እና በተሸናፊ የዜሮ ድምር ቀመር ከማስላት ይልቅ፣ አካታችነትን፣ የጋራ ውሳኔን፣ ተመጣጣኝ ውክልናን እና የሥልጣን ክፍፍልን ማዕከል ያደረገ ሥርዓት ነው።
ይህ ሥርዓት በዋናነት የምዕራቡ ዓለም ከሚከተለው “የአብላጫ ዴሞክራሲ” (Majoritarian Democracy) በእጅጉ ይለያል። በአብላጫው የሊበራል ዴሞክራሲ ሞዴል 50 ሲደመር አንድ (50%+1) ድምፅ ያገኘ የፖለቲካ አካል የመንግሥትን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር፣ የተሸናፊው ድምፅ ከውሳኔ ሰጪነት ይገለላል።
ይህ ዓይነቱ አሠራር ባህላዊ እና ሀገራዊ መግባባት በዳበረባቸው፣ እንዲሁም አንጻራዊ የኅብረተሰብ ተቀራራቢነት ባለባቸው ሀገራት ሊሠራ ቢችልም፤ ጉልህ ብሔራዊ እና ፖለቲካዊ ልዩነት ባለባቸው ኅብረ ብሔራዊ ሀገራት ግን ወደ አግላይነት እና ወደ ‘የብዙኃን ጭቆና’ ያመራል።
በተቃራኒው የመግባባት ዴሞክራሲ የድርድር፣ የተዋስኦ (Deliberative) እና የጥምረት ፖለቲካን የሚያራምድ በመሆኑ፣ የትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ወይም የፖለቲካ ቡድን በሀገር አስተዳደር ውስጥ ድምፁ እንዳይታፈን ትልቅ መዋቅራዊ ዋስትና ይሰጣል።
ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸው ሀገራት ተሞክሮ
የመግባባት ዴሞክራሲን አስፈላጊነት በተግባር ለመረዳት ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን እና በብዝኃነት የተሞሉ ሀገራትን ተሞክሮ መቃኘት እጅግ ጠቃሚ ነው።
ለምሳሌ ስዊዘርላንድን ብንወስድ፤ በውስጧ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች እና የሃይማኖት ልዩነቶች ቢኖሩባትም፣ ሀገሪቱ የምትመራው ሁሉንም ባካተተ "ታላቁ ቅንጅት" (Grand Coalition) ሞዴል በመሆኑ ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት በሰላም ዘልቃለች።
በተመሳሳይ፣ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ሥርዓት ስትወጣ የተካረረውን የዘር ልዩነት ለማስታገስ ኔልሰን ማንዴላ የመሩት ፓርቲ ፍጹም አብላጫ ድምፅ ቢያገኝም ሀገሪቱን ከእልቂት ለመታደግ ሲሉ ተቃዋሚዎችን ያካተተ "የብሔራዊ አንድነት መንግሥት" መሥርተዋል።
ልጅየም እና ሊባኖስም የተሰነጠቀ ማኅበራዊ መዋቅራቸውን ለመጠገን የተጠቀሙት ይኸው የመግባባት ዴሞክራሲን ነው። እነዚህ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች በግልጽ የሚያሳዩት፣ ልዩነቶች የሰፉባቸው ሀገራት ሕልውናቸውን የሚያስቀጥሉት በፉክክር እና በመገፋፋት ብቻ ሳይሆን በመደመር እና በመግባባት መሆኑን ነው።
የመግባባት ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ እና ሀገራዊ መሠረቶቹ
ኢትዮጵያ ለመግባባት ዴሞክራሲ የሚያስፈልጉት ሁለቱም ዋነኛ መነሻ ገጽታዎች አሏት፤ ይኸውም የልዩነት ተግዳሮቶች እና የጋራ አብሮነት እሴቶች (ኢትዮጵያዊ ወረቶች) ናቸው።
የሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ የብቸኛ አሸናፊነት እና አግላይነት ባህል የጎላበት በመሆኑ፣ ይህን ታሪካዊ ስብራት ለመጠገን እና ዘላቂ ብሔራዊ ቅቡልነት (Legitimacy) ለማምጣት ሥልጣን መጋራትን የሚያበረታታ ሥርዓት በእጅጉ ያስፈልገናል።
ሐቁ ደግሞ ኢትዮጵያ የመግባባት ዴሞክራሲን ከውጭ አስመጥታ መትከል አያስፈልጋትም፤ ምክንያቱም የዚህ ሥርዓት ጽኑ እርሾ በሀገር በቀል እሴቶቻችን ውስጥ በሚገባ ይገኛል።
መንግሥት ይህንን እውን ለማድረግ ከወሰዳቸው ቁርጠኛ እርምጃዎች አንዱ የፖለቲካ ምኅዳሩን በራስ ተነሣሽነት ማስፋቱ ነው። እንደ ማሳያ ገዥው ፓርቲ 85 በመቶ መቀመጫ ላይ ብቻ በመወዳደር 15 በመቶውን ለተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት የመተው አቋም ማንጸባረቁ በፖለቲካ ታሪካችን የዴሞክራሲ ቁርጠኝነት መገለጫ ሆኖ አልፏል።
በተጨማሪም፣ ከተፎካካሪ ፓርቲ የተውጣጡ በርካታ ምሁራን እና ፖለቲከኞች በካቢኔ እና በተለያዩ የአመራር እርከኖች ሥልጣን ተጋርተው እንዲሠሩ መደረጉ የዚሁ ሥርዓት ተግባራዊ አካል ነው።
ከዚህም ባለፈ የዜሮ ድምር ፖለቲካን ለማክተም የዘመናት የታፈኑ ጥያቄዎችን እና የተካረሩ ልዩነቶችን በሰላማዊ፣ አሳታፊ እና አካታች መንገድ ለመፍታት “ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን” ተቋቁሞ በመላ ሀገራችን ወደ ተግባር መግባቱ የመግባባት ዴሞክራሲን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
በአጠቃላይ ሲታይ፣ የመግባባት ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና እና የዘላቂ ሰላም ዋስትና ጉዳይ ነው። ያለፈውን የፖለቲካ ስብራት ጠግነን ጠንካራ የሲቪክ ብሔርተኝነት እና የጋራ ማንነት መገንባት የምንችለው “አሸናፊ ሁሉንም ይወስዳል” ከሚለው የፉክክር ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ ወጥተን ወደ ተዋስኦ፣ ትብብርና መግባባት ስንሸጋገር ብቻ ነው።
በመሆኑም፣ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት የሞራል እና ባህላዊ እሴቶች መሠረት ያደረገው “ኢትዮጵያዊ የመግባባት ዴሞክራሲ” የጀመርነውን የሪፎርም እና አብሮ የማደግ ጉዞ ከዳር ለማድረስ እጅግ አስተማማኝ እና ምሁራዊ መሠረት ያለው ብቸኛ ፍኖት ነው።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: