ነገ በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት ቀን (መውሊድ) በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት፣ በፍቅር እና በደስታ በድምቀት ይከበራል።
በዓሉ የታላቁን ነቢይ ሕይወት፣ መልካም አርዓያነትና አስተምህሮ የምንዘክርበት ነው።
መንደሮች በመንዙማ (በነቢዩ ሙሐመድ ውዳሴ) ድምፅ ሲደምቁ፣ የመኖሪያ ቤቶች ደጃፎች በቡና እና በዕጣን መዓዛ ሲታወዱ፣ የደስታ መንፈስ እያንዳንዱን ማዕዘን ይሞላዋል።
በመስጂዶች፣ በታሪካዊ ሐድራዎች እና በመኖሪያ ቤቶች የነቢዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ምጡቅ ስብዕና፣ ገድል፣ ፍቅርና እዝነት የሚዘክሩ መንዙማዎች (ውዳሴዎች) ይከናወናሉ።
በሀገራችን የመውሊድ በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን እንደጠበቀ፣ ከተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ ትውፊቶች ጋር ተዋህዶ የሚከበርበት መንገድ ለየት ያለ ኅብረ-ብሔራዊ ውበትን አጎናፅፎታል።
ከሐረር ጀጎል ታሪካዊ ግንቦች እስከ ወሎ የእስልምና ትምህርት ማዕከላት፣ ከጅማና ባሌ ሐድራዎች እስከ አዲስ አበባ መስጂዶች በዓሉ በየአካባቢው በድምቀት ይከበራል።
በየመንደሩ የሚደረጉ የጋራ ማዕድ ዝግጅቶች እና መስተንግዶዎች የኢትዮጵያውያንን የቆየ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።
መውሊድ ከመንፈሳዊነቱ በተጓዳኝ አቅመ-ደካሞችን በመደገፍና ማዕድ በማጋራት እንዲሁም የቲሞችን (ወላጅ አልባ ህፃናትን) በማስደሰት የማህበራዊ ትስስር እና የአብሮነት ገመድን እያጠናከረ ያለ ነው።
የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የሰላም፣ የፍትህ እና የሰብዓዊነት አስተምህሮ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና አንድነት አስፈላጊ እሴት በመሆኑ፣ ይህን ታላቅ በዓል ስናከብር ልዩነቶችን በመደማመጥና በምክክር በመሻገር ሊሆን ይገባል።
መልካም የመውሊድ በዓል!
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: