በማንኛውም ሀገራዊ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ልዩነቶች መኖራቸው ተፈጥሯዊ ነው። ነገር ግን የእነዚህ ልዩነቶች መገለጫ እና ማስተናገጃ መንገድ የሀገርን እጣ ፈንታ ይወስናል።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የማያግባቡን ጉዳዮች ካሉ በሰላማዊ፣ በሰለጠነ የፖለቲካ አግባብ መነጋገር ይቻላል፤ ከዚያ ውጪ ያለው አማራጭ ኢትዮጵያን አይጠቅምም" በሚል ያስተላለፉት መልዕክት ይህን እውነታ የሚያስገነዝብ ነው።
ይህ መልዕክት አሁን ላይ ሀገራችን ለምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ እንደ ትልቅ መፍትሔ እና ማሳሰቢያ ሊወሰድ የሚገባው ነው።
ለመሆኑ "በሰለጠነ የፖለቲካ አግባብ መነጋገር" ሲባል ምን ማለት ነው? ከሱ ውጪ ያለው አማራጭስ በምኑ ነው ኢትዮጵያን የማይጠቅመው? በጥልቀት እንፈትሸው።
የሰለጠነ የፖለቲካ አግባብ
የሰለጠነ ፖለቲካ ማለት ልዩነትን በጠረጴዛ ዙሪያ፣ በሐሳብ ብልጫ እና በሰላማዊ ክርክር የመፍታት ጥበብ ነው።
ይህ አካሄድ ሦስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ያሉት ሲሆን፣ የመጀመሪያው ለመደማመጥ ዝግጁ መሆን ነው።
ይህም የራስን ሐሳብ ብቻ ትክክል አድርጎ ከመውሰድ ወጥቶ፣ የሌላውን ወገን ስጋትና ፍላጎት በሰላም ማዳመጥ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ የሕግ የበላይነትን ማክበር ሲሆን፣ ማንኛውም የፖለቲካ ጥያቄ ወይም ተቃውሞ በሰላማዊ እና ህጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያመላክታል።
የጋራ ጥቅምን ማስቀደም ሦስተኛው ነጥብ ሲሆን፣ ይህም ከቡድን ወይም ከግል የፖለቲካ ትርፍ ይልቅ የሀገርን ሰላም እና የሕዝብን ደኅንነት ማዕከል ማድረግ መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳል።
ባለፉት ዓመታት በሀገራችን የታዩት ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች በተግባር እንዳሳዩን ከሰላማዊ ንግግር ውጪ ያሉ አማራጮች ማለትም ኃይልን የመጠቀም አባዜ ያስገኙልን ትርፍ የለም።
ይልቁንም የሀገርን የሰው ኃይል እና በከፍተኛ ጥረት የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን ወደ ማውደም ያመራል።
ኢንቨስትመንት እንዲሸሽ፣ የዋጋ ንረት እንዲያሻቅብ እና የዜጎች ዕለታዊ ኑሮ እንዲመሰቃቀል በማድረግ አሉታዊ ተጽዕኖን እንደሚያሳድር የሚታወቅ ነው።
አንዱ በኃይል ሌላውን ለማንበርከክ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ሀገራዊ አንድነት ይሸረሸራል፤ ለትውልድ የሚተርፍ የቂም በቀል አዙሪት ይፈጠራል።
ስለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ከዚያ ውጪ ያለው አማራጭ ኢትዮጵያን አይጠቅምም" ሲሉ በግልጽ ቋንቋ የገለጹት። ኃይል መፍትሄ ሳይሆን የችግሮች ሁሉ ምንጭ መሆኑንም ነው መልዕክታቸው የሚያስገነዝበው።
ከቃላት ወደ ተግባር
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት መሬት ወርዶ ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ ከሁሉም ወገን ተግባራዊ ምላሽን ይሻል።
መንግሥት ለሰላማዊ እና ለሰለጠነ የፖለቲካ ክርክር የሚሆኑ ምህዳሮችን ይበልጥ ማስፋት ሁሉንም አካታች የሆኑ የውይይት መድረኮችን እንደ ሀገራዊ ምክክር ያሉትን ማጠናከር እና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ይኖርበታል።
እንዲሁም የፖለቲካ ፍላጎቶችን በኃይል ወይም በሕዝብ እልቂት ለማስፈጸም ከመሞከር መቆጠብ አማራጭ ሐሳቦችን በሰለጠነ መንገድ ለሕዝብ ማቅረብ እና በምርጫ ካርድ ብቻ ሥልጣንን ለመያዝ መሥራት።
የጥላቻ ንግግሮችን በማስወገድ የሰላም እና የውይይት ባህል በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ ማንኛውም የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት አዘጋጆች የበኩላቸውን አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳረፍ የተሻለው አማራጭ ነው።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ አሁን ላይ ካለችበት ውስብስብ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ሰላማዊ ውይይት የቅንጦት ምርጫ ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰነዘሩት ሐሳብ የሁላችንም የዘወትር መርህ ሊሆን ይገባል።
ልዩነቶቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ መፍታት ስንችል ብቻ ነው ጠንካራ፣ የበለፀገች እና ከስጋት ነፃ የሆነች ኢትዮጵያን መገንባት የምንችለው።
የሐሳብ የበላይነት እንጂ የክንድ የበላይነት ሀገርን አያሻግርም!
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: