ነገ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስና እጅግ ታላቅ ምዕራፍ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነች «የዛሬ ምክክር፤ የነገ ፅኑ ሀገር፤ የጥል አጥር ፈርሶ፤ የሰላም ድልድይ የሚገነባበት የጋራ ሀገራዊ ምክክር፣ ዘመናትን የተሻገሩ መዋቅራዊ ስንጥቆቻችንን በውይይት የምንጠግንበት ታላቅ የሰላም መድረክ ነው።
በሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪካችን ውስጥ ያልተፈቱ የቅራኔ ምንጮችና የተጋጩ ትርክቶች ሀገራዊ ህልውናችንን በተደጋጋሚ ሲፈታተኑት ኖረዋል።
ባለፉት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣን ሽግግር በተደረገ ቁጥር መዋቅራዊ ክፍተቶችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ተቋማዊ ልምድ ማነሳችን የልሂቃን አለመደማመጥን አግዝፎ፣ የጽንፍ ፖለቲካን በማስፋፋትና የታችኛውን ህዝብ ድምፅ በማፈን ሀገራችንን የሁከትና የጦርነት አውድማ አድርጓታል።
ይህንን ዘመናትን የተሻገረ የታሪክ ጠባሳ ለመፈወስ ታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ እጅግ አድካሚና ውስብስብ የሆኑ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎችን በብቃት ሲያከናውን ቆይቶ አሁን ለታላቁና ወሳኙ የምክክር ጉባኤ ምዕራፍ በቅቷል።
የኮሚሽኑን ሰነዶችና አጠቃላይ የዝግጅት ምዕራፍ እንደሚያሳየዉ ሂደቱ ፍፁም አካታችና ህዝባዊ መሆኑን እንረዳለን። ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ከ200 ሺህ በላይ ተወካዮች በቀጥታ እንዲሳተፉ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን እውነተኛ ውክልና ያረጋገጠ ነው። በሂደቱ ከ50 በላይ በሚሆኑ ሀገራት የሚኖሩ የዲያስፖራ አባላትም በዲጂታል አማራጮች ሐሳባቸውን አጋርተዋል።
ይህ የጂኦግራፊያዊ ተደራሽነት ስፋት፣ ከ1 ሺህ 300 በላይ ከሚሆኑ ወረዳዎች የተውጣጡ ጥሬ አጀንዳዎችን በስልታዊ መንገድ ለማደራጀት አስችሏል። እነዚህ አጀንዳዎች በሕገ-መንግሥትና በመንግሥት መዋቅር፣ በታሪክ ትርክቶችና በኢኮኖሚና ሀብት ክፍፍል እንዲሁም በማንነት ጥያቄዎችና ሌሎች ዙሪያ በዋና ዋና ስልታዊ ጭብጦች መከፋፈላቸው ስር የሰደዱ መዋቅራዊ ህመሞች በትክክል የሚፈትሹ መሆናቸውን ያሳያል።
ይህ ታሪካዊ መድረክ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ አዲስ ስልጣኔን የፈጠረ ተጨባጭ እመርታ ነው። ልዩነቶችን በኃይል ከመፍታት ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ የመደማመጥ ባህልን በማስረፅ፣ ተራው ዜጋ ከመንደርና ከወረዳ ተነስቶ ያለምንም ጫና ሀሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ይፈጥራል።
ከዚህ ቀደም እርስ በርስ እንደ ጠላት ይተያዩ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ዛሬ በአንድ መድረክ ተቀምጠው በጋራ አጀንዳዎች ላይ ሲወያዩ ማየት የፖለቲካ ውጥረትን በመቀነስ ረገድ ታላቅ ስነ-ልቦናዊ እፎይታን ሰጥቷል።
የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት የሂደቱ ትክክለኛ ስኬትና ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የሚለካው ነገ በሚጀመረው በዚህ ማሳረጊያ ምዕራፍ በሚደረሱ ስምምነቶች ጥራትና ተግባራዊነት ላይ ነው።
ሂደቱ ወደ ማጠናቀቂያው ብሔራዊ ጉባኤ በሚሸጋገርበት በዚህ ወቅት ሶስት ዋና ዋና የቀጣይ ስትራቴጂዎች ላይ ማተኮር ግድ ይላል። አንደኛው፣ ከህዝቡ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን መሰረት በማድረግ ግልጽና ገለልተኛ የውሳኔ ሃሳቦችን ማርቀቅ ነው።
ሁለተኛውና እጅግ ወሳኙ ጉዳይ እነዚህን የውሳኔ ሃሳቦች ወደ ህግ፣ ፖሊሲና ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ለመቀየር የሚያስችል የመንግስትና የፖለቲካ ኃይሎች የላቀ ቁርጠኝነት ነው።
ሶስተኛው ኮሚሽኑ ተልዕኮውን ሲያጠናቅቅ የተደረሱት ስምምነቶች በትክክል መሬት ላይ መውረዳቸውን የሚከታተል በህግ ስልጣን የተሰጠው ገለልተኛ የትግበራ አካል ማቋቋም ነው።
ምክክሩ በአንድ ጀንበር ሁሉንም የትላንት ቁስል የሚፈውስ አስማተኛ በትር ባይሆንም ዴሞክራሲያዊትና ሰላማዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የተቀመጠ መሰረት ነው።
በመሆኑም ነገ የሚጀመረው ብሔራዊ ምክክር የጥል አጥርን አፍርሶ የሰላም ድልድይ በመገንባት፣ የራሳችንን ችግር በራሳችን ጠረጴዛ ፈተን ለቀጣዩ ትውልድ የምትሻገር ፅኑ ሀገር የምናስረክብበት ታላቅ የወርቅ ምዕራፍ ሆኖ በታሪክ መዝገብ ላይ በደማቁ ይከተባል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: