ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ውስብስብ ከሆኑባት የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ ችግሮች ለመውጣት የጀመረችው አዲስ የመፍትሔ አካል የሆነው ሀገራዊ ምክክር፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የሚሳተፉበትን ዋናውን የውይይት መድረክ ለመጀመር በመጨረሻ ቀናት ላይ ይገኛል።
ለዘመናት የዘለቁ የሐሳብ ልዩነቶችን፣ የታሪክ ቁስሎችን እና የፖለቲካ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትልቅ ሀገራዊ ተስፋ የተሞላ ነው።
ይህ መድረክ እናቶች ልጆቻቸው በፍቅርና በትብብር የሚኖሩባትን ሀገር እንዲያልሙ ከማድረጉም በላይ፣ ድምፃቸው ያልተሰማ ወገኖች የሚሰሙበት የፍትሕና የፖለቲካ መረጋጋት ቁልፍ መፍትሔ ተደርጎ እየተገመገመ ይገኛል። ሂደቱ የታለመውን ግብ መምታት የሚችለውም ሁሉም አካል የሂደቱ ባለቤት እና ጠባቂ መሆን ሲችል ብቻ ነው።
ይህ ምክክር ነገ የምትገነባውን የተረጋጋች ሀገር እውን ለማድረግ የተያዘ ትልቅ መፍትሔ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደቱ ተዓማኒ፣ ገለልተኛ እና አካታች እንዲሆን በማድረግ በስኬት እያከናወነ ይገኛል።
ዛሬ በውይይት ጠረጴዛ ዙሪያ የምናሳየው መደማመጥ እና የምናንጸባርቀው መቻቻል ለነገዋ ኢትዮጵያ አዲስ ንጋትና አስተማማኝ ተስፋን የሚወልድ የሰለጠነ መንገድ ነው።
ይህ ሀገራዊ ምክክር ልዩነቶችን ለመፍታት መሠረት የሚጥል፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማጎልበት ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ባሕልን የሚያዳብር፣ ያደገና የተለወጠ ሥርዓት ባለቤት ለመሆን በዜጎች መካከል የተሻሻለ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር እና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት እጅግ ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: