Search

የኢትዮጵያ ባሕር በር ጥያቄ የህልውና፣ የብሔራዊ ክብር እና የቀጣናዊ ዘላቂ ሰላም ዋስትና

ማክሰኞ ሐምሌ 07, 2018 138

የኢትዮጵያና የቀይ ባሕር ታሪክ ሊነጣጠል የማይችል የህልውና የሥልጣኔና የብልጽግና ምንጭ መሆኑን ተከትሎ ሀገራችን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ የምትወጣበት የባሕር በር ማግኘቷ የቅንጦት ሳይሆን ቀጣዩን ትውልድ ካልተገባ የትራንስፖርት ወጪና ከኢኮኖሚ ተግዳሮት ለማዳን የሚደረግ ታሪካዊና የብሔራዊ ክብር ጥያቄ ነው።

በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሳቢያ ሁልጊዜም የጂኦፖለቲካ ፍላጎቶች መናኸሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ በዚህ ቀጣና ውስጥ ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት የባሕር በር አልባ መሆኗ የራሷን የኢኮኖሚ እድገት ከመገደቡ ባለፈ በቀጣናው መረጋጋት ላይ የራሱ ተጽእኖ አለው።

የባሕር በር አለመኖር የሀገርን የንግድ እንቅስቃሴ በመገደብ ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግና ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴን በሌሎች ሀገራት መልካም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያደርግ ሲሆን ኢትዮጵያም በታሪክ አጋጣሚ ልክ ባልነበረ ፖለቲካዊ ውሳኔ የባህር በሯን ካጣች በኋላ የውጭ የንግድ እንቅስቃሴዋ በጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በየዓመቱ ለቢሊዮን ዶላሮች ወጪ እየተዳረገች ትገኛለች።

በመሆኑም ይህ ሕዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰንበት እንደ ሀገር የማደግ  የመበልጸግ እና ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር የፍትሀዊነት ጥያቄ የራስ ወዳድነት ፍላጎት ሳይሆን የሕዝቦቿ እድገት ልማት የወጣቶች ሥራ ፈጠራ እና እንደ ሀገር የህልውና ጉዳይ ነው።

ሀገራት በኢኮኖሚ እርስ በርስ የሚኖራቸው ትስስር በጠነከረ ቁጥር በመካከላቸው የመተማመንና የመተባበር መንፈስ በርትቶ የግጭት ዕድል በእጅጉ የሚቀንስ ሲሆን ለኢትዮጵያ ቀጥተኛ የባሕር በር ካላት የምርት ወጪዋ ቀንሶ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱና ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ታላቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

የባሕር በር ባለቤት የሆኑ ሀገራት የንግድ ጂኦፖለቲካዊና ቀጣናዊ ጥቅምን ለማስከበር በነጻነት የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ ኢትዮጵያም ጠንካራ የባሕር ኃይል እና የወደብ መዋቅር ሲኖራት በቀጣናው የሚስተዋሉትን የባሕህር ላይ ወንብድና እና የሽብርተኝነት ስጋቶች ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለመከላከል ሰፊ አቅም ይፈጥራል ይህም ሕገ ወጥ ስደት እና የወንጀል ተጋላጭነት በእጅጉ ይቀንሳል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የዓለም አቀፍ የባሕር ሕግን እና የጋራ ልማት መርሆዎችን መሠረት ያደረገ ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት የሀገራችንን የልማት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ ቀጣናዊ ትስስርን የሚያፋጥን እና ለመላው አፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ዋስትና የሚሰጥ ነው።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: