Search

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ሁለት የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ

ማክሰኞ ሐምሌ 07, 2018 139

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባው፣ ለሀገራዊ መዋቅራዊ ሽግግርና ለዘርፉ ልማት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን ሁለት የብድር ስምምነቶች በአዋጅ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በዕለቱ ውሎው መጀመሪያ የተመለከተው በኢትዮጵያና በጣሊያን ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል የተፈረመውን የ70 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት ነው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) የብድር ስምምነቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ይህ የረጅም ጊዜ ቀላል ብድር ሙሉ በሙሉ ከወለድና ከአገልግሎት ክፍያ ነፃ ሲሆን፣ የ16 ዓመት የእፎይታ ጊዜን ጨምሮ በ30 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው።

ብድሩ ከዓለም ባንክ ለሦስተኛው የኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት ፖሊሲ ክንውን ጋር በተጣጣመ መልኩ በቀጥታ ለመንግሥት የበጀት ድጋፍ ማስፈጸሚያና ኢትዮጵያ ለጀመረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚውል በመሆኑ ዕድገትን ለማፋጠን የላቀ ፋይዳ እንዳለው ተገልጾ፣ ምክር ቤቱም ረቂቁን በጥልቀት መርምሮ በአዋጅ ቁጥር 1438/2018 በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በፈረንሳይ መንግሥት መካከል የተደረገውን የ54 ሚሊዮን 600 ሺህ ዩሮ የብድር ስምምነት መርምሮ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

ይህ የብድር ስምምነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና የትዕዛዝ ቁጥጥርና የንብረት አስተዳደር ሥርዓቶችን የደረጃ አወጣጥ የዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክት ለማስፈጸም የሚውል ነው።

የብድር ስምምነቱ የ10 ዓመታት የእፎይታ ጊዜ ያለውና በ25 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ የወለድ መጠኑም 0 ነጥብ 347 በመቶ ዝቅተኛ መጠን ያለው መሆኑ ተገልጿል።

ብድሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ትራንስሚሽኖችንና ሰብስቴሽኖችን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ፣ የጥገና ሥራዎችን ለማጠናከር፣ የቁጥጥር ማዕከላትን አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለመገንባትና የኢዮጵያን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ለማፋጠን ታላቅ አቅም እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

ምክር ቤቱ ይህንን ረቂቅ አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 1439/2018 በሙሉ ድምፅ ያጸደቀው ሲሆን፣ የተገኙት እነዚህ የብድር ስምምነቶች የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እያሳየ የመጣውን ጥንካሬና ዕድገት በተግባር የሚያሳዩ እንደሆኑ ተብራርቷል።

በሂሩት እምቢአለ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: