Search

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የቀረበለትን ሀገራዊ ጥሪ በደስታ ተቀብሎ ይተገብራል፦ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ማክሰኞ ሐምሌ 07, 2018 290

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ግቢ በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እንዲሁም የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።

በመርሃ ግብሩ ወቅት እንደተገለጸው፣ ሠራዊቱ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በአጠቃላይ 20 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዷል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ መከላከያ ሠራዊት አገሩን በብቃት ከመጠበቅ ጎን ለጎን ችግኞችን የመትከል የቆየ ባህል ያለው ተቋም ነው። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም የሠራዊቱን ይህንን በጎ ባህል ይበልጥ እንዳጠናከረው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ አካል እንደመሆኑ መጠን፣ የቀረበለትን ሀገራዊ ጥሪ በደስታ ተቀብሎ ከቀጠናው ነዋሪዎች ጋር በመቀናጀት የችግኝ ተከላውን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በመጨመርና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመከላከል ረገድ ተጨባጭ ውጤቶችን እያመጣ እንደሚገኝ የገለጹት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ሠራዊቱ ይህንን ሀገራዊ ኃላፊነት በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በአባዲ ወይናይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: