Search

አረንጓዴ ዐሻራ ከተፈጥሮ ሚዛን ጥበቃ እስከ ብዝሃ ሕይወት ልማትና ዘላቂ ተጠቃሚነት

ማክሰኞ ሐምሌ 07, 2018 106

ኢትዮጵያ የዘመናት የደን መመናመንን ለመቀልበስ የጀመረችው ግዙፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሀገራችንን ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የዲፕሎማሲ ከፍታ እያሸጋገራት ይገኛል።

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በየደረጃው ሲተገበር በቆየው በዚህ ንቅናቄ እስካሁን ድረስ ከ48 ቢሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የደን የፍራፍሬ እና የመኖ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን ይህም የሀገራችን የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ በማድረስ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ የሙቀት አማቂ ጋዞችን የመያዝ አቅሟን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።

በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የዓለም አቅጣጫዎች የሚሰሙት የሙቀት ማዕበል የደኖች መቃጠል እና የውኃ አካላት መድረቅ የአየር ንብረት ለውጥ አስቸኳይ አደጋ መሆኑን በሚያሳዩበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ የተፈጥሮ ሚዛንን ለመመለስ እንደ ትልቅ ማሳያ እና ተስፋ የሚቆጠር ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ንቅናቄ ሆኗል።

ይህ ሰፊ መርሀ ግብር ከተራ የችግኝ ተከላ ዘመቻነት ተሻግሮ ዛፍ መትከልን የሕልውና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በቢሊዮኖች የሚገመት የካርበን ፋይናንስ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድሎችን የሚከፍት የልማት ስትራቴጂ በማድረግ ረገድ ግዙፍ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ትርጉም አግኝቷል።

ንቅናቄው መሬት እንዳይሸረሸር የከርሰ ምድር ውኃ እንዲያገግም የሥነ ምህዳር ሚዛን እንዲጠበቅ እንዲሁም በከተሞች አካባቢ የኮንክሪት እና የአስፋልት ሙቀት ነጸብራቅን በመከላከል የአየር ንብረቱን በማቀዝቀዝ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደቱን እያፋጠነው ይገኛል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬቷን እንደ ዲፕሎማሲያዊ መሣሪያ እየተጠቀመችበት ሲሆን የቀጣናውን አረንጓዴ ልማትና ድንበር ተሻጋሪ ትብብር በተግባር እያጠናከረች ትገኛለች።

ይህም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች የኢትዮጵያን ተሞክሮ ሌሎች ታዳጊ ሀገራት ሊከተሉት የሚገባ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ትምህርት የሰጠ ትልቅ አሻራ ነው።

በመሆኑም ለነገዋ አረንጓዴና ለምለም ኢትዮጵያ ሁሉም የበኩሉን አሻራ በተግባር በማሳረፍ በሀገር ደረጃም ሆነ በግለሰብ ሕይወት ላይ እያሳደረ ያለው ዘላቂና አዎንታዊ ተፅዕኖ በላቀ ሁኔታ እንዲሳካ መላው የህብረተሰብ ክፍል ችግኝ ከመትከል ባለፈ የተተከሉ ችግኞችን በባለቤትነት ስሜት ማሳደግና እስኪጸድቁ ድረስ ተከታታይ እንክብካቤና ጥበቃ የማድረግ ብሔራዊና ማኅበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል።

በብሌን ደምበሎ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: