የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የ2018 ዓ.ም. በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን የገመገመ ሲሆን፣ በዚህም ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ፓስፖርት፣ ከ1 ሚሊዮን በላይ ቪዛ፣ 32 ሺህ 952 የትውልደ ኢትዮጵያውያን መታወቂያ እንዲሁም 21 ሺህ 163 ጊዜያዊና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ በመስጠት ስኬታማ አፈጻጸም ማስመዝገቡን አስታውቋል።
ከተሰጡት በእነዚህ አገልግሎቶች በአጠቃላይ ከ42 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፣ በአየርና በየብስ ድንበር ለ7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ገቢና ወጪ መንገደኞች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጉዞ ሰነድ አገልግሎት ተሰጥቷል።
ከዚህም ባሻገር በሲቪል ምዝገባ ረገድ ከ6 ሚሊዮን በላይ የልደትና ሌሎች ኩነቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከሕገወጥነት መከላከል አንጻርም በሐሰተኛ ሰነድ ሲያጭበረብሩ የተገኙ 433 የውጭ ዜጎችና 4 ሺህ 450 ኢትዮጵያውያን ተይዘው ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል።
በተጨማሪም 21 ሕገወጥ ደላሎች እና በኦንላይን የአስቸኳይ ፓስፖርት ምዝገባ ላይ ማጭበርበር የፈጸሙ 174 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ ከድርጊቱ ጋር የተገናኙ 24 ቤቶችም ታሽገዋል።
የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከነባር 12 ወደ 23 በማሳደግ የኢ-ፓስፖርት አገልግሎትን በክልሎችና በአዲስ አበባ በተሳካ ሁኔታ መተግበር መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፣ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ለዚህ ተደራሽነት ትልቅ እምርታ ሆኗል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ተቋሙ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሁሉም ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን ጠቅሰው፣ ለዚህ ስኬትም የቆየውን አሮጌ ሲስተም ሙሉ በሙሉ በመቀየር በዋናው መሥሪያ ቤትና በቅርንጫፎች አዲስ የኔትወርክ ዝርጋታ በማጠናቀቅ ወደ አዲስ የዲጂታል ሲስተም መሻገሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም የአሠራሮች ዲጂታላይዝ መሆን፣ የአመራሩና የባለሙያው ቁርጠኝነት እንዲሁም የተከታታይ ሥልጠናዎች መሠጠት ለውጤቱ መሠረት መሆናቸውን መግለጻቸውን የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: