Search

ወረርሽኞችን በፍጥነት መከላከል የሚያስችል የላብራቶሪ ማዕከል ተገንብቷል፡- የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

ማክሰኞ ሐምሌ 07, 2018 126

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተመሠረተበትን 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከመጪው ሐሙስ ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ከሕዝብ ጋር በይፋ እንደሚያከብር አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ የምስረታ በዓሉን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ተቋሙ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በርካታ የላብራቶሪ ምርምር ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ አዳዲስ በሽታዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዘመናዊ የላብራቶሪ ምርምር ማዕከል መገንባት መቻሉን ይፋ አድርገዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ተቋሙ ድንበር ተሻጋሪ ለሆኑ የጤና ስጋቶች አፋጣኝ የክትትል፣ የቅኝትና የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው እንደ ማርበርግ ቫይረስ፣ ኤምፖክስ (Mpox) እና ሌሎች አዳዲስ ተከስተው የነበሩ ወረርሽኞችን በሕብረተሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ ቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር መቻሉ ነው።

ኢንስቲትዩቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሱን በዘመናዊ የላብራቶሪ ቴክኖሎጂዎች በመገንባት ዜጎችን ከተላላፊና ከተለያዩ ወረርሽኞች የመታደግ ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

"የኢንስቲትዩቱ መቶኛ ዓመት በዓል ተቋሙ ያለፈባቸውን አስቸጋሪ ውጣ ውረዶችና ያስመዘገባቸውን ታላላቅ ስኬቶች የምናስብበት  ነው" ሲሉ ዶ/ር መሳይ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡

ይህ ታሪካዊ የምስረታ በዓል በሚከበርበት ወቅት 5ኛው የሕብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኮንፈረንስን ጨምሮ የተለያዩ ሳይንሳዊና ማኅበራዊ ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ ይጠበቃል።

አንጋፋ የሆነው ኢንስቲትዩቱ ከመጀመሪያው የ"ተፈሪ መኮንን ሆስፒታል" ስያሜ ጀምሮ የተለያዩ መዋቅራዊና ስያሜ ለውጦችን በማድረግ፣ በአሁኑ ወቅት "የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት" በመባል የኢትዮጵያውያንን ጤናና ደህንነት የመጠበቅ ታላቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

በመሃሪ ዓለሙ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: