Search

ታሪካዊው ምዕራፍ፦ የቆዩ ቁርሾዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት 4 ሺሕ ተመካካሪዎች በአዲስ አበባ ይመካከራሉ

ረቡዕ ሐምሌ 08, 2018 141

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ስታከናውን የቆየችው እና መላው ሕዝብ በትዕግሥት ሲጠብቀው የነበረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፣ ወደ መጨረሻው እና ወሳኙ ምዕራፍ በመሸጋገር በአዲስ አበባ ከደቂቃዎች በኋላ ይጀመራል።

ይህ ጉባኤ ያለፉ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ቁርሾዎችን በምክክር በመፍታት፣ ጠንካራ የጋራ ሀገር ለመገንባት የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ወሳኝ ቁልፍ መሆኑን ምሁራን እየገለጹ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በአጀንዳ ማሰባሰብ እና በተሳታፊዎች ልየታ ላይ ሰፊ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፣ ዛሬ ለሚጀመረው ታላቅ ጉባኤ ከሁሉም የሀገራችን ማዕዘናት የተወከሉ 4 ሺሕ ተመካካሪዎች በመዲናዋ ተገኝተዋል።

ተመካካሪዎቹ በዝርዝር መክረው ዘላቂ መፍትሔዎችን ያስቀመጡባቸዋል ተብለው በኮሚሽኑ ይፋ የተደረጉት ስምንት ዐበይት አጀንዳዎች የሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀት እና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች (አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ) ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት እና ሰብአዊ መብቶች፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ እንዲሁም ሙስና፣ መልካም አስተዳደር እና የሰላም ግንባታ ናቸው።

ይህ መድረክ ለኢትዮጵያውያን የተሰጠ ታላቅና ታሪካዊ ዕድል ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን የቆዩ ቁርሾዎችንና የማያስማሟቸውን ጉዳዮች ሁሉ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ግልጽ ንግግር መፍታት የሚያስችላቸው ነው።

ምሁራን እንደሚሉት፣ ሀገራዊ ምክክሩ ከማንኛውም መሣሪያ በላይ ትልቅ ፋይዳ እና ጉልበት ያለው ሒደት ሲሆን፤ በተለያዩ ክልሎች እና በአዲስ አበባ የተደረጉት የቅድመ ዝግጅት ውይይቶች የፈጠሩት መቀራረብ እና መተማመን ለዛሬው ጉባኤ ትልቅ ብርታት ነው።

ውስብስብ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በምክክር ብቻ በመሆኑ፣ ጉዳዩ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም ይገልጻሉ።

ይህ ታሪካዊ ጉባኤ በኢትዮጵያ ታሪክ የቆዩ እና ሥር የሰደዱ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ለምክክሩ ውጤታማነት እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት።

የምክክሩ መጀመር በመላ ሀገራችን ከፍተኛ ተስፋን ያጫረ ሲሆን፣ ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ ታላቅ ዕድል በመሆኑ፣ ዕድሉ እንዳይባክን የሁሉም ወገን ንቁ አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው።

በአጀንዳም ሆነ በተመካካሪዎች ስብጥር ረገድ ኮሚሽኑ መላዋን ኢትዮጵያን በአግባቡ የወከለ በመሆኑ፣ የተለዩት አጀንዳዎች በሚገባ ከተመከረባቸው ልዩነቶችን ፈትቶ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ዋስትና ይሆናል።

ይህ ምክክር ያለፉት ዓመታት ስብራቶች በጋራ እሳቤ የሚጠገኑበት በመሆኑ፣ ለሚቀጥለው ትውልድ የተሻለች እና የተከበረች ኢትዮጵያን ለማስረከብ የሚያስችል የጋራ ትርክት እንደሚፈጠርም ታምኖበታል።

ዛሬ የሚጀመረው እና ሁሉንም ወገኖች አሸናፊ እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ይህ ታላቅ መድረክ፣ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ አንድነት እና ሁለንተናዊ ልማት አዲስ ታሪካዊ መሠረት ይጥላል።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: