ዛሬ በይፋ የሚጀምረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለሀገራችን ኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት ትልቅ ኹነት ነው።
ለዘመናት የዘለቁ የፖለቲካ ልዩነቶችን፣ የማንነት ጥያቄዎችን እና የጋራ ታሪክ ግንባታ ክፍተቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የተጀመረው ይህ ታላቅ መድረክ፣ የሁላችንንም ትኩረት እና እገዛ የሚሻ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
ይህ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሕልውና እና ሰላም ለመገንባት ጠንካራ መሠረት የሚጥል ትልቅ መድረክ ሲሆን፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና በዋና ዋና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስን ዓላማ አድርጓል።
የግጭት ምንጮችን በዘላቂነት በማድረቅ የልዩነት ድምፆችን በውይይት እና በሐሳብ የበላይነት በመተካት የኃይል አማራጭን ማስቀረትን እንዲሁም ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን የሚያፋጥኑ እና የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጡ የጋራ ስምምነቶችን ማመንጨት ከጉባኤው ዓላማዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የምክክር ጉባኤው ከመላው የሀገራችን ክፍሎች የተወከሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ እኩል የሚሰማበት መድረክ ነው።
ለዘመናት በጠብመንጃ አፈሙዝ እና በፖለቲካ ሴራ ለመፍታት የተሞከሩ ውስብስብ ችግሮች ዛሬ በሠለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በሐሳብ የበላይነት ለመፍታት የተዘጋጀ መድረክ መሆኑም ጉባኤውን ልዩ ያደርገዋል።
በመድረኩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ እና ቁርጠኝነት፣ የማኅበረሰብ መሪዎች እና የሃይማኖት አባቶች የሕዝብን እሴትና ባህል መሠረት ያደረገ እርቅ ለማውረድ እንዲሁም ወጣቶች እና ሴቶች የነገዋን ኢትዮጵያ የሚረከቡ አካላት እንደመሆናቸው ለስኬቱ ያላቸው ሚና የጎላ ነው።
ይህ ታላቁ የምክክር ጉባኤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ወይም የፖለቲከኞች ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰንበት መድረክ ነው።
ዛሬ የሚጀምረውን ይህንን ታሪካዊ ጉባኤ ስኬታማ ለማድረግ እያንዳንዳችን በሐሳብ ከመደገፍ፣ ገንቢ የሆኑ አስተያየቶችን ከመስጠት እና መድረኩን ከሚያደናቅፉ አሉታዊ ፕሮፓጋንዳዎች ከመቆጠብ ጀምሮ የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል።
ዛሬ የምንዘራው የምክክር፣ የመደማመጥ እና የሰላም ዘር ነገ ለልጆቻችን የምታፈራ፣ የበለጸገች እና የተረጋጋች ሀገርን ያስረክበናል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: