Search

ልዩነትን በሐሳብ ማረቅ

ረቡዕ ሐምሌ 08, 2018 107

 የሥልጣኔ፣ የዴሞክራሲና የጋራ አሸናፊነት ልዕልና

የሰው ልጅ ከጋርዮሻዊ የጉልበት ጽልመት ወጥቶ የብርሃን ዘመን ላይ መድረሱን ከሚያመላክቱት ታላላቅ ማሳያዎች መካከል፣ ልዩነትን በሐሳብ የማረቅ ጥበብ ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል።

በጡንቻ መተማመን የድንቁርና ማሳያ ሲሆን፣ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ የሐሳብ ሙግት ማድረግ ግን የሥልጣኔ ሁሉ ማማ ነው።

አንድ ስልጡን ማኅበረሰብ የሚለካው ልዩነቶች በመጥፋታቸው ሳይሆን፣ እነዚያን ተፈጥሯዊ የሐሳብ፣ የአመለካከት እና የፍላጎት ልዩነቶች በሚያስተናግድበት የረቀቀ የጥበብ መንገድ ነው።

የሥልጣኔ እና የሰለጠነ ማኅበረሰብ ግንባታ

ታላላቅ ሥልጣኔዎች የግንባታ መሠረታቸው ስልጡን እና ከዘመናቸው የሚሻገሩ ትውልዶች ናቸው።

ትውልዶች የሥልጣኔ ማዕከላትን ከመገንባት እና ቴክኖሎጂን ከማምጠቅ ባሻገር፣ በመጀመሪያ የሰው ልጅን አእምሮ ማነጽ ነው።

የሰው ልጅ እውነተኛ ሥልጣኔ የሚረጋገጠው፣ ግጭቶችን እና ተቃርኖዎችን ከጦር ሜዳ አውድማ አውጥቶ ወደ ምሁራዊ የክርክር መድረክ ሲያሸጋግራቸው ነው።

ልዩነትን በሐሳብ ማረቅ መቻል ዜጎች በጠላትነት ከመፈላለግ ይልቅ በወንድማማችነት መንፈስ እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ፣ ሀገራዊ መግባባት እንዲያብብ እና ስልጡን ማኅበረሰብ እንዲገነባ ያደርጋል።

ሐሳብን በሐሳብ መሞገት የሰለጠነ ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት ቋንቋ እንጂ የቅንጦት ጉዳይ አይደለም።

ዴሞክራሲን ማጥለቅ

ከዚህም ባለፈ፣ ልዩነትን በሐሳብ ማረቅ ዴሞክራሲን ከሥረ መሠረቱ የማነጽ እና የማጽናት ሕያው መገለጫ ነው።

ዴሞክራሲ በመሠረቱ የሐሳብ ብዝኃነትን ማክበር እና የተለየ ድምፅን ማዳመጥ ነው። "አሸናፊ ሁሉንም ይወስዳል" ከሚለው ኋላቀር የዜሮ ድምር ፖለቲካ ወጥቶ፣ የሁሉንም ወገን ሥጋት እና ፍላጎት ያማከለ የመግባባት ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ የሐሳብ ልዕልና ወሳኝ ነው።

ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት የሚገነቡት፣ የፖለቲካ ባሕላችን ከጠመንጃ አፈሙዝ ቋንቋ ተላቆ በምክንያታዊነት እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ሲቃኝ ብቻ ነው።

በጋራ ማሸነፍ እና ዘላቂ ዕድገት

በዚህ ስልጡን የሐሳብ መድረክ ውስጥ እውነተኛው ድል "በጋራ ማሸነፍ" ነው። ልዩነትን በሐሳብ አርቀን፣ ተደማምጠን እና ተቻችለን ስንወጣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተሸናፊነት ስሜት አይኖርም፤ ሁሉም ዜጋ የውሳኔው ባለቤትና የሀገሩ ባለድርሻ መሆኑን በኩራት ይቀበላል።

አንዱ ወንድም ሌላውን አንገት በማስደፋት የሚያገኘው ዘላቂ እና እውነተኛ ድል የለም። ሀገር የምትጸናው፣ ዕድገትም መሬት የሚነካው ሁላችንም የሐሳባችንን ድርና ማግ አዋህደን፣ አንዱ የሌላውን ክፍተት ሞልቶ በጋራ አሸናፊ ስንሆን ነው።

በሐሳብ መሸናነፍ ውስጥ የሚፈጠር የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ዕድገት ዜጎች በነፃነት የሚፈጥሩበት እና የሚያድጉበት ሰፊ ሜዳ ይከፍታል።

ሀገራችን ከገባችበት የፖለቲካ አዙሪት ወጥታ ወደ ላቀ የሥልጣኔ ማማ እንድትሻገር፣ ልዩነትን በሐሳብ የማረቅ ጥበብን የሕልውናችን መሠረት ልናደርገው ይገባል።

የሐሳብ ልዕልና ሲነግሥ የልዩነት አጥር ላይ የተንጠለጠለው ኋላቀርነት ይሸነፋል፣ መደማመጥ ሲሰፍን የጥላቻ ግድግዳ ይናዳል።

ሁላችንም አሸናፊ የምንሆንበትን፣ ዴሞክራሲያችን የሚፀናበት እና ማኅበረሰባችን የሰለጠነበትን ብሩህ ዘመን ለማየትልዩነትን በሐሳብ አርቀን በጋራ ማሸነፍን ብቸኛ የልዕልናችን መንገድ እናድርገው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: