በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና የሀገራችንን የዘመናት ስብራቶች ለመጠገን ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
ጉባኤው በክፍፍል እና በቁርሾ ውስጥ የመዳከርን ምዕራፍ በመዝጋት፣ በመቻቻል እና በውይይት ላይ የተመሠረተች አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ያለመ የትውልድ ዕዳ መክፈያ ጅማሮ ነው።
የዚህ ምክክር ዋና ዓላማ ሥር የሰደዱ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የማንነት ክፍፍል ችግሮችን በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በውይይት ብልኃት መፍታት ነው።
ዛሬ በጠረጴዛ ዙሪያ የሚታየው ቅንነት እና የሚወሰኑት ውሳኔዎች የወደፊቱን የሀገር አንድነት፣ ሰላም እና የጋራ ብልጽግና የሚወስኑ በመሆናቸው፣ መድረኩ ታሪካዊ ቁስሎችን ለማከም እና ሀገራዊ እርቅን ለማስፈን የተገኘ ወርቃማ ዕድል ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እንደ የልሂቃን ጥርጣሬ፣ የአካባቢ ግጭቶችና የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች ያሉ በርካታ ተግዳሮቶችን አልፏል።
ሆኖም ኮሚሽኑ እነዚህን ፈተናዎች በጽናት በመቋቋም፣ በሁሉም ክልሎች እውነተኛ አሳታፊነትን ያረጋገጡ ውይይቶችን በማካሄድ ዛሬ ለደረሰበት ታሪካዊ ምዕራፍ መብቃቱ ተነግሯል።
ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች መማር እንደሚቻለው ብሔራዊ ምክክር ፈጣን እና በአንድ ጀምበር የሚጠናቀቅ ሳይሆን ረጅም ጊዜን፣ ታላቅ ትዕግሥትን እና የፀና እምነትን የሚጠይቅ የትውልድ ኢንቨስትመንት ነው።
የዛሬው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ጅማሮ የፍጻሜ ማረጋገጫ ሳይሆን በእምነት እና በቅንነት መጓዝ የሚያስፈልግ የረጅም መንገድ መጀመሪያ እርምጃ እንደሆነ ተመላክቷል።
በአሁኑ ወቅት የምክክር ጠረጴዛውን የያዙት ተመካካሪዎች የሀገርን ሕልውና የተሸከሙ በመሆኑም፣ ለሰላም አላስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚጥሉ እና በምክክር ላይ የዋጋ ተመን የሚያስቀምጡ አካላትን ወደ ጎን በመተው፣ ለጋራ ሀገራዊ ራዕይ ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸው ጥሪ ቀርቧል።
ሰላም፣ መከባበር እና ትብብር የመጪዋ፣ የዴሞክራሲያዊቷ እና የበለጸገችው ኢትዮጵያ መሠረት ይሆኑ ዘንድ የዘመናችን ትልቁ ምዕራፍ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: