Search

ቱሪዝም አዲሱ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መዘውር

ዓርብ ሐምሌ 10, 2018 175

በዘመናዊው የዓለም ፖለቲካ መድረክ፣ የአንድ ሀገር ተሰሚነት እና ስልታዊ ተፅዕኖ የሚለካው በወታደራዊ ወይም በኢኮኖሚ ግዝፈት (Hard Power) ብቻ አይደለም።

ከዚህ ይልቅ ሀገራት ባላቸው ባህላዊ ማራኪነት፣ ታሪካዊ እሴት እና በጎ ገጽታ ማለትም 'በለስላሳ ኃይል' (Soft Power) አማካኝነት ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ እየሆኑ መጥተዋል። ለዚህ ደግሞ ቱሪዝም ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል።

በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጥናቶች መሠረት ቱሪዝም "የዜጎች ዲፕሎማሲ" በመባል ይታወቃል።

አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ሀገራችንን ሲጎበኝ፣ ከባህላችን እና ከሕዝባችን ጋር ቀጥተኛ ትስስር ይፈጥራል። ወደ ሀገሩ ሲመለስም የኢትዮጵያ የክብር አምባሳደር በመሆን አዎንታዊ ገጽታችንን ይመሰክራል።

በዓለም አቀፉ የለስላሳ ኃይል መለኪያ (Global Soft Power Index) ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ሀገራት የቱሪዝም ዘርፋቸው እጅግ የዳበረ መሆኑ ቱሪዝም ለዲፕሎማሲው ስኬት ያለውን ተጨባጭ ሚና ያረጋግጣል።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዲፕሎማሲ በተግባር ስኬታማ እየሆነ መምጣቱን በቅርቡ በአዲስ አበባ የሚገኙ እና 40 በላይ ሀገራትን እንዲሁም 10 ዓለም አቀፍ ተቋማትን የወከሉ አምባሳደሮች በታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ያደረጉት ጉብኝት አንዱ ማሳያ ነው።

ዲፕሎማቶቹ የቅርስ ጥበቃ ሥራዎችን ከመጎብኘት ባለፈ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በቅጥር ግቢው ውስጥ ችግኞችን ተክለዋል።

ይህ ተግባር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት በማሳየት፣ አስተማማኝ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የቱሪስት መዳረሻ መሆኗን ለዓለም ያበሰረ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ ነው።

አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እና የዓለም ዲፕሎማቶች መቀመጫ በመሆኗ ሦስተኛዋ የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከል ተብላለች፡፡ ይሁን አንጂ ከዚህ ቀደም ወደ ስብሰባ የሚመጡ መሪዎች ከስብሰባ አዳራሽ ውጭ የሚጎበኙት ማራኪ ስፍራ እምብዛም አልነበረም።

ይህንን ክፍተት ለመቅረፍ የተከናወኑት ሰፊ የከተማ ኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይረውታል።

በተጨማሪም በአንድ ጊዜ እስከ 10 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችለው ዘመናዊው አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መገንባቱ፣ የጉባኤ (MICE) ቱሪዝምን በማሳደግ ረገድ ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

ባለፈው ዓመት ብቻ 150 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማስተናገዳችን እንዲሁም እንደ "አይሾው ስፒድ" እና "ደይላን ፔጅ" ያሉ ታዋቂ የዲጂታል ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መምጣት የሀገራችንን ደኅንነት እና ውበት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ተመልካቾች አስተዋውቋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አነሳሽነት የተጀመሩት "ገበታ" ፕሮጀክቶች አዲሱ የቱሪዝም ስትራቴጂያችን ዋነኛ ሞተሮች ሆነዋል።

የውጭ ዲፕሎማቶች የነዚህን ስፍራዎች ብሎም የሐረር እና ድሬዳዋ የኮሪደር ልማቶችን መጎብኘታቸው የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማስፋፋት ባለፈ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር አድርጓል።

በዘንድሮው ዓመት በመጀመሪያዎቹ 9 ወራት ብቻ 1.2 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ሀገራችንን የጎበኙ ሲሆን፣ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

50 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችም ሀገራቸውን ጎብኝተዋል። ይህ የዘርፉ ዕድገት የኢኮኖሚ ጥንካሬን ከመፍጠር አልፎ፣ የኢትዮጵያን የጂኦ-ፖለቲካ ተደራዳሪነት አቅም በማሳደግ በብሪክስ (BRICS) አባልነት ማዕቀፍ እና በቀጣናዊ ዲፕሎማሲ ውስጥ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋር እንድትሆን አስችሏታል።

ኢትዮጵያ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም ይበልጥ እንድታገኝ የዲያስፖራውን ተሳትፎ ማጠናከር፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችን ማስፋፋት እና ማኅበረሰብ-ተኮር ቱሪዝምን ማበረታታት ይጠበቅባታል።

በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: