Search

ተመካክሮ መላቅ ወይንም ተለያይቶ መናቅ

ዓርብ ሐምሌ 10, 2018 211

ወደኋላ መለስ ብለን ዘመናዊ የሀገረ መንግሥት ግንባታ (State-building) ታሪካዊ ሂደታችንን ስንመረምር፣ ኢትዮጵያ የዘመናዊ ሥልጣኔ እና የሀገር ግንባታ እርምጃዋን የጀመረችው ዛሬ ላይ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ የዓለማችን ግዙፍ ከሆኑት እንደ ጃፓን እና ኮሪያ ካሉ ሀገራት ጋር እኩል፣ አልፎ ተርፎም ቀድማ ነበር።

በእርግጥም የዘመናዊ ሀገረ መንግሥት ምስረታችንን እንደ ጀርመን (.. 1871 እንደተዋሐደችው) እና ቻይና ካሉ ታላላቅ የዓለማችን ሀገራት የለውጥ ዘመን ጋር ተቀራራቢ በሆነ የታሪክ አጋጣሚ (19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽና ማብቂያ ላይ) ጀምረን ነበር።

ቀድማ የባቡር ቴክኖሎጂን ያስተዋወቀችው፣ ዘመናዊ አየር መንገድን በጊዜ የመሰረተችው እና ለዘመናዊ ሥልጣኔ በሯን የከፈተችው ሀገራችን፣ ዛሬ በምን ደረጃ ላይ ትገኛለች?

እነዚያ እኛ ስንጀምር የጀመሩ፣ እኛ ስንነሳ አብረው የተነሱ ሀገራት ተመካክረው እና የጋራ ራዕይ ሰንቀው ወደ ከፍታ ሲልቁ እኛስ ለምን በድህነት አዘቅት ውስጥ ወደኋላ ቀርተን የዓለም መሳቂያና መናቂያ ሆንን?

መልሱ አጭር፣ ቁልጭ ያለ እና በማያሻማ ሁኔታ ግልፅ ነው፤ ዋነኛው ምክንያት ቆም ብሎ ባለመመካከራችን፣ የጋራ ሀገራዊ ራዕይ ባለመያዛችን እና የውስጥ የፖለቲካ ቁርሾ ውስጥ እስከ አንገታችን በመዘፈቃችን ነው።

ሀሳባችንን በአንድ ገበታ ላይ አቅርበን ተመካክረን ከመላቅ ይልቅ እያንዳንዳችን በየፊናችን ተበታትነን መናቅን መረጥን።

ይህ የኋላቀርነት ልምምዳችን ደግሞ ከጥንት ማንነታችን እና እሴታችን ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነው።

ኢትዮጵያ ከጥንት የዘመን ማለዳ ጀምሮ፣ ማኅበራዊ ውጣ ውረዶቿን በዋርካ ሥር ሸንጎ እና በሰለጠነ የዕርቅ ሥርዓት ስታክም የኖረች እጅግ የዳበረ የምክክር እሴት ያላት ታላቅ ሀገር ናት።

አባቶቻችን በዛፍ ጥላ ሥር ተቀምጠው፣ የተጣላን በማስታረቅ፣ የተቆጣን በማብረድ እና የጎበጠን በማቅናት ሀገርን አፅንተው አቆይተውናል። ይሁን እንጂ፣ ባለፉት መቶ ዓመታት የተጓዝንበት የፖለቲካ መንገድ የዚህን እሴት ተቃራኒ ገፅታ በጉልህ አሳይቶናል።

ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅ እና አብሮ ከመምከር ይልቅ፣ ተበታትኖ እና ተለያይቶ መናቅ በሀገራችን የፖለቲካ ባህል ውስጥ ነግሶ ቆይቷል።

የተለየ ሀሳብን ማራመድ እንደ ጠላት የሚያስቆጥርበት፣ ልዩነትን ይዞ መወያየት እንደ ትልቅ ኃጢአት የሚታይበት የጨለማ ዘመን ውስጥ በብዙ መከራ አልፈናል።

"ድር ቢያብር አንበሳ ያስር" እንደሚባለው፣ አንድነታችንን አጠናክረን ስለጋራ ቤታችን መነጋገር ሲገባን፣ በመከፋፈላችን እና በመለያየታችን ምክንያት ለውጭ ጠላቶቻችን የጥፋት ሴራ የተመቸን ሆንን።

የሀብታችን ምንጭ እና የህልውናችን መሰረት የሆኑትን ታላላቅ ገፀ በረከቶቻችንን፣ በተለይም ዓባይን የመሳሰሉ ገደብ የለሽ የውኃ ጸጋዎቻችንን በነፃነት አልምተን እንዳንጠቀም የጠላት መጠቀሚያ እና ማሳለጫ ሆንን።

እርስ በርስ ስንናቆር፣ ከገዛ ሀብቶቻችን ርቀን የድህነትን ፅዋ ለመጠጣት ተገደድን። እውነታው እንደ ፀሀይ የሚያንፀባርቀው እዚህ ላይ ነው፤ ሳንመካከር ስንቀር፣ ተበታትነን ስንለያይ በጠላት እንናቃለን፣ እንደከማለን። በተቃራኒው ደግሞ፣ ስንመካከር፣ ስንነጋገር እና ስንደማመጥ እንደ አለት እንበረታለን፣ አቅማችን ይጎለብታል፣ እንዲሁም ሀብታችንን አልምተን ማደግ እና ከፍታ ላይ መላቅ እንችላለን።

ዛሬ ላይ ቆመን፣ ይህ የተበታተነ ሀሳብ እና አውዳሚ ግጭት ያመጣብንን ተለያይቶ የመናቅ የኋሊት ጉዞ በውል ልንገነዘብ ይገባል።

"በመመካከር የተሰራ አጥር ነፋስ አይፈታውም" እንዲሉ አበው፣ አሁን በፊታችን በሰፊው የተዘረጋው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ይህንን የታሪክ እና የፖለቲካ ስብራት የምንጠግንበት ወደር የለሽ አጋጣሚ ነው።

ተበታትነን ከመቅረት፣ ተለያይተን ከመናቅ እና የጠላት ሲሳይ ከመሆን ወጥተን፣ ዛሬውኑ በቅንነት ተመካክረን እጅግ የበለፀገች፣ ከፍታ ላይ የላቀች ውድ ኢትዮጵያን ለልጆቻችን በጋራ እንገንባ።

ያለፉት የስህተት ዘመናት ትምህርት ሆነውን፣ ተመካክሮ ከመላቅ የሚገኘውን ታላቅ በረከት አጥብቀን ይዘን፣ ወደ ብሩህ ተስፋችን በአንድነት እናምራ!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: