የጉምሩክ ኮሚሽን ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 429.7 ሚሊዮን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና 11.2 ሚሊዮን ብር የወጪ፤ በድምሩ 440.9 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተይዘዋል።
ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል አዳዲስ እና አልባሽ ጨርቆች፣ ቡና፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የግንባታ ዕቃዎች፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ ዕፆች፣ መድኃኒት፣ ማዕድናት እና የውጭ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል።
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ እና የወጪ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር አዲስ አበባ ኤርፖርት፣ ጅግጅጋ እና አዋሽ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ፣ በቅደም ተከተላቸውም 118 ሚሊዮን፣ 111 ሚሊዮን እና 82 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መያዝ ችለዋል።
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሠራተኞች፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ኅብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በጥቆማ እና በበረራ የተያዙ ሲሆን፣ የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 28 ተጠርጣሪዎች እና 15 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የሕግ ማስከበር ሥራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሠራተኞች እና አመራሮች፣ የክልልና የፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ እንዲሁም ለመላው ሕዝብ ምስጋናውን አድርሷል።
የኮንትሮባንድ እና ሕገ ወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ፣ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን አቅርቧል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: