Search

ምክክርን ከጦርነት ያስበለጠው የኢትዮጵያ ጉዞ እና የኢጋድ አጋርነት

ዓርብ ሐምሌ 10, 2018 121

ኢትዮጵያ አሁን የጀመረችው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ስኬት ለመላው ምሥራቅ አፍሪካ ብሎም ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ታላቅ ተምሳሌት እና የሰላም ሞዴል እንደሚሆን በርካቶች ይስማማሉ፡፡

የአፍሪካ ቀንድ በታሪኩ በውክልና ጦርነት፣ በድንበር ግጭት እና በውስጥ አለመረጋጋት ሲታመስ የኖረ ቀጣና ነው።

በዚህ ቀጣና ውስጥ ማዕከላዊ የስበት ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ ውስብስብ የሆኑ የፖለቲካ ልዩነቶቿን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት እና በመደማመጥ መፍታት ከቻለች ይህ አብነት የቀጣናውን የፖለቲካ ትርክት መሰረታዊ በሆነ መንገድ ይቀይረዋል።

ይህ ስኬት ሌሎች ጎረቤት ሀገራትም የጦር መሳሪያቸውን አስቀምጠው የኃይል አማራጭን በመተው ወደ ሀገራዊ ምክክር እንዲመጡ የሚያስገድድ ታላቅ የሞራል ልዕልናን ይፈጥራል።

በዚህ እውነት ላይ በመቆም የምሥራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (/) በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ያላትን ጥልቅ የእርቅ እና የይቅርታ ባህል እንዲሁም የሽማግሌዎች ጥበብ መጠቀም እንጂ መፍትሔ ፍለጋ ወደ ውጭ ማማተር የለባትም፡፡

የራሳችንን ቁስል የምናክምበት ቁልፍ በእጃችን እንዳለ አስገንዝበው ይህ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ከመቀነስ ባለፈ ችግራችንን ራሳችን በሀገራዊ ምክክር መፍታት እንችላለን የሚል ሥነ-ልቦናዊ ልዕልናን የሚገነባ ነው።

የአፍሪካ ቀንድ በተለይም ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሰለባ ሆና መቆየቷን በመገንዘብ ልዩነትን በኃይል ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ውድቅ ማድረግ እንዳለብን አበክረው ገልጸዋል ዋና ጸሐፊዉ።

በግጭት የተገነባ ሀገር የለም ያሉት ዋና ፀሐፊ / ወርቅነህ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን የትግል ስልታቸውን ወደ ስልጡን ክርክር እና ምክክር እንዲቀይሩ እና ልዩነቶቻቸውን በብዕር ኃይል እና በውይይት መፍታት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ይህ የምክክር ጉባኤ ሂደት ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተተወ ሳይሆን ቀጣናዊ ዕውቅና እና ድጋፍ ያለው መሆኑን ተቋማቸው ኢጋድ ከኢትዮያ ጋር እንደሚቆም ባስተላለፉት መልዕክት አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በውይይት ችግሮቿን መፍታቷ የአፍሪካ ቀንድ ወደ ብሩህ ተስፋ የሚመራበት ዓይነተኛ እርምጃ መሆኑን ማመላከታቸውም፣ የኢትዮጵያ ሰላም ለጠቅላላው ቀጣና ተሻጋሪ የሆነ የሰላም አብነት እንደሚሆን በግልጽ ያሳያል።

ዋና ፀሐፊው የኢትዮጵያ ታሪክ ወደፊት የሚሠራው በመነጋገር መሆኑን በማስመር የፖለቲካ ኃይሎች ማንኛውንም ጉዳይ በውይይት እና በመመካከር እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ጉባኤ የኢትዮጵያን ተስፋ የሚያለመልም ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድን የፖለቲካ ትርክት ከግጭት ቀጣናነት ወደ በውይይት ችግር ፈቺነት የሚቀይር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አሁን ኃላፊነቱ ያለው "ብዕርን ከጥይት፣ ውይይትን ከጦርነት" አስበልጠው አዲሲቷን ኢትዮጵያ በሚገነቡት ዜጎችና ልሂቃን እጅ ነው።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: