ከደቡብ ኦሞ ዞን፣ ሐመር ወረዳ፣ ከካራ ብሔረሰብ የመጣችው ሙዶ አኮ፣ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መድረኩ ላይ ስትቆም እጆቿ በትንሹ ይንቀጠቀጡ ነበር።
ሆኖም በደረቷ ውስጥ የሚመታው ልቧ በማይነጥፍ ተስፋ እና በፅኑ አቋም ተሞልቷል።
ለዓመታት በዝምታ ታፍኖ የኖረውን የብዙ እናቶች እምባና ምኞት በውስጧ ሰንቃለች።
"ዛሬ በፊታችሁ የቆምኩት እንደ አንዲት ተራ ኢትዮጵያዊት እናት ብቻ ሳይሆን የሰላም ተምሳሌት በመሆን ነው" በማለት የጀመረችው ንግግር፣ የአድማጭን ልብ ሰርስሮ በመግባት ድባቡን በቅፅበት ቀየረው።
ለዘመናት እሷ እና መሰል የተዘነጉ እናቶች፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ እና የታሪክ ውጣ ውረድ ከሩቅ ቆመው ከመመልከት የዘለለ ሚና አልነበራቸውም።
ሌሎች ሲናገሩ፣ ሌሎች ሲወስኑ፣ እነሱ ከዳር ሆነው በዝምታ ታዝበዋል። በግጭት እና ባለመግባባት የሚሞቱት ልጆቻቸው እና ወንድሞቻቸው ናቸው፤ ሀዘኑን የሚሸከሙት፣ አስክሬን የሚቀብሩትና እምባ የሚያብሱት እነሱው ናቸው።
"መቼ ይሆን ሰላም የሚመጣው?" እያሉ በተስፋ መቁረጥ እና በመጓጓት መካከል ሆነው ቢጠይቁም፣ የሚመልስላቸው አልነበረም።
ዛሬ ግን የዘመናት ዝምታ ተሰብሯል። ሀገሯ እንድትናገር ጠርታታለች፤ ሙዶም ጥሪውን ተቀብላ የሁሉንም እናቶች ልብ በሚወክል አንደበት ድምጿን አሰማች።
የሙዶ ድምፅ የራሷ ብቻ አልነበረም። ማንም ያልሰማቸው፣ ማንም ያላማከራቸው፣ ነገር ግን ከዘመናት በፊት ጀምሮ ኢትዮጵያን ከልባቸው የወደዱ የብዙ ሚሊዮን እናቶች የጋራ ጩኸት እንጂ።
ዛሬ ኢትዮጵያ ይህንን ከልብ የመነጨ የእናቶች ድምፅ በፅሞና እያዳመጠችው ነው። እውነታው ፍንትው ብሎ ወጥቷል፤ባለመነጋገራችን እና ባለመደማመጣችን እንደ ሀገር ብዙ አጥተናል።
እስካሁን ባለው የልዩነት ጉዟችን ያተረፍነው እምባ፣ መቃብር፣ ጥላቻ፣ ሀዘን እና በቀልን ብቻ ነው።
"እሳት በማቀጣጠል ቤት መገንባት ቢቻል ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት ተገንብታ እና በልፅጋ ትጠናቀቅ ነበር!" ሙዶ ይህንን ሀቅ ነው ያስገነዘበችው።
እውነተኛ እና ፅኑ ቤት የሚገነባው እጆች ሲተባበሩ እና ልቦች በቅንነት ሲደማመጡ ብቻ መሆኑን በተግባር ልናየው ይገባል።
እናት ሙዶ ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗን አስረግጣ በመናገር፣ ወገኖቿ በልባቸው ይዘውት የመጡትን ቁጣ፣ ቂም እና ቋጠሮ እንዳያረግዙት እና ይዘው እንዳይመለሱ ተማፀነች።
በአንድ ማዕድ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መመካከርን፣ የልብን ቋጠሮ በውይይት እና በይቅርታ መፍታትን የዘመኑ ብቸኛ መፍትሔ አድርጋ አቀረባለች።
"ከእንግዲህ ወዲህ 'ማን ያሸንፋል? ማን ይረታል?' ብለን መጠየቅ ማቆም አለብን። ከእኛ ወይም ከቡድናችን ማሸነፍ ይልቅ፣ ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ!" ይህ የሙዶ አኮ እና በየጓዳው የሚያነቡ የብዙ ሚሊዮን እናቶች ብቸኛ ህልምና ፀሎት ነው።
የልዩነትን ግድግዳ አፍርሰን፣ ቁጣን አብርደን፣ ሁላችንም አንድ ላይ ሆነን እናታችን ኢትዮጵያን አሸናፊ የምናደርግበት ጊዜ አሁን ነው። መፍትሄው በእጃችን፣ ምርጫውም የኛው ነው!
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: