በአበው ጥልቅ ፍልስፍና እና በታላላቅ ጸሐፍት ምናብ ውስጥ የሰው ልጅ ተፈጥሮ እጅግ አስገራሚ ሆኖ ይሳላል።
አንዳንዱ ዓይን እያለው ማየት፣ ጆሮ እያለው መስማት ይሳነዋል፤ ብርሃን ሲፈነጥቅ "ለምን በራ?" ጨለማ ሲወድቅ "ለምን መሸ?" ማለትን የሕይወት ቋሚ ዜማው ያደረገ ጥቂት አይደለም።
ሀገር ስትለማ፣ የብልጽግናን ጎዳና ስትጀምር እና የትላንት ማነቆዋን ስትበጥስ "አይ... ውኃ ቀጠነ" እያሉ ማነወር መገለጫቸው የሆኑ ነቃፊዎች ሁሌም አሉ።
በተለይም ርዕሰ ከተማችን አዲስ አበባ የዘመናት አቧራዋን አራግፋ፣ እንደ አዲስ ሙሽራ ስታሸበርቅ እና ዓለም አቀፍ ገጽታዋን በውበት ስትቀይር ስም እየሰጡ ከውበቱ እና ከዕድገቱ በላይ ክፉ ገፅታ እንዲጎላ ለማድረግ የሚሞክሩ "ከተማ ፈረሰ፣ መልክ ጠፋ፣ ታሪክ ተናደ፣ ሕዝብ ተፈናቀለ" እያሉ የዋይታ እንባ የሚያነቡ፣ የለውጡን ጸዳል በጥርጣሬ መነጽር የሚያዩ አልጠፉም።
ባጭሩ ኢትዮጵያ ሠርታ ልትለወጥ አልባሌነትን አውልቃ ልትጥል ወገቧን ስታስር፤ ስኬቷ አልጠማቸው፣ ለውጧ አልጣፍጣቸው ብሎ ሲያማርሩ ይስተዋላል።
ዛሬ ደግሞ ሀገራችን የዘመናት የፖለቲካ ስብራቷን ለመጠገን፣ የተመረቀዘ ቁስሏን በገዛ ልጆቿ እጅ ለማከም ታሪካዊ የምክክር ማዕድ ስትዘረጋ እነዚሁ ኃይሎች በለመዱት የፌዝ ዜማ አደባባይ ወጥተዋል።
"የምን ምክር ነው? ኢትዮጵያ እኮ እየመከረች አይደለም!" እያሉ በማሾፍና በማናናቅ እውነታውን ለማጠልሸት ይሞክራሉ።
ነገር ግን፣ እነርሱ በማሾፍ እና በማውገዝ አዙሪት ውስጥ ሲንገዋለሉ ኢትዮጵያ ግን ዛሬም እንደ ትላንቱ አንገቷን ደፍታ ያደሩ የቤት ሥራዎቿን በጽናት እየሠራች ነው!
አዎ፣ ኢትዮጵያ በትውልዱ እና በዘመኑ ሊወጣ የሚገባውን ከባድ የቤት ሥራ እንደ ውኃ ኩልል ብሎ በሚፈስ ጥበብ እና በተግባር እያከናወነች ትገኛለች።
የብዙ መቶ ዘመናት የዕዳ ክምችት፣ የትውልዶች የቁርሾ ቋጠሮ በጥቂት ዓመታት ውስጥ እየተወራረደ እና እየተፈታ ነው።
ያለፉ ቁስሎቿን በዘላቂነት ለመሻገር ኢትዮጵያ ዛሬ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በሯን ዘግታ በገዛ ልጆቿ አቅም እየመከረች እና እየተነጋገረች ነው።
ማንም በማንም ዕጣ ፈንታ ላይ በጉልበት በማይወስንበት፣ የሁሉንም ልጆቿን እኩል እና ፍትሐዊ ተሳትፎ ባረጋገጠ መድረክ ላይ ነች።
ይህ ምክክር በማስገደድ ሳይሆን፣ በልጆቿ የከረመ የልብ ፍላጎት፣ በበጎ ፈቃደኝነት እና ከልብ በመነጨ ሀገራዊ የኃላፊነት ስሜት የሚመራ እውነተኛ የመታደስ ጉባኤ ነው።
እርግጥ ነው ወሬ የፈታው የሚለውን ብሒል ይዘው በወሬ ናዳ ጉዞውን ለማስቆም መሞከር፣ ማጥላላት ሥራ ከተባለ ማውገዝ እና ማናናቅ ሞያ ከተባለ ሌሊት ተቀን ሥራቸውን እየሠሩ ነው፡፡
ነገር ግን መታወቅ ያለበት አንድ ገዘፍ ያለ ሐቅ አለ፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ የኢትዮጵያን ጉዳይ፣ እንዲሁም የሀገራችንን መሠረታዊ ፍላጎት አንዳችም ምድራዊ ኃይል ሊነካው አይችልም።
ኢትዮጵያ ወሬ የማይፈታት ታላቅ የሀገር ግንባታ ጉዞ ላይ ነች!! በዓድዋ፣ በአምስቱ ዓመት የፋሺስት ውጊያ ባንዳዎች በወሬ ብዛት ኢትጵያን እንዳልረቱ ሁሉ ይህ የዛሬው ትውልድም የጀመረውን ታሪካዊ ጉዞውን ከግብ በማድረስ የሀገሩን ዕጣ ፈንታ በጽኑ መሠረት ላይ ከማቆም አንዲትም ስንዝር ወደ ኋላ አይልም። የትናንት አውዳሚ ትርክቶች የኢትዮጵያን የሥራ መንፈስ አያደነዝዙትም።
"ውሾች ይጮኻሉ" በሚለው ተረት አንዳንዶች አየር ላይ ሆነው የራሳቸውን ጩኸት ቢያስተጋቡም ኢትዮጵያ ግን ከፍታዋን አትተውም።
ኢትዮጵያ ሥራዋን ትሠራለች! የዕድገት፣ የሰላም እና የብልጽግና ጉዞዋም ፈጽሞ ሳይገታ ወደፊት ይቀጥላል! የነቃፊዎች ጩኸት አየር ላይ ሲተንን የኢትዮጵያ ልጆች በምክክር ያነጹት ሀገራዊ አብሮነት ግን ዘመናትን ተሻግሮ ጸንቶ ይኖራል።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: