የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ ረጅም ቢሆንም፣ አብሮት የዘለቀ ሥር የሰደደ መዋቅራዊ የፖለቲካ ስብራት ይታይበታል።
የሐሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ከማስተናገድ ይልቅ፣ በኃይለ ቃል ጀምሮ በጉልበት የመደምደም አውዳሚ ልማድ ሀገራችንን ዋጋ ሲያከፍላት ኖሯል።
ይህ አዙሪት ባለፉት ዐሥርት ዓመታት የትውልድን አቅም የበላ፣ ለሀገራዊ መግባባት ጋሬጣ የሆነ እና ለውጭ ጫና በር የከፈተ ነው።
ዛሬ ግን ይህንን የታሪክ ስብራት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመጠገን የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግረው ታሪካዊው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመድረኩ መክፈቻ ላይ ያስተላለፏቸው መልዕክቶች ይህንን ሀገራዊ ራዕይ በሚገባ የሚያስተሣሥሩ ናቸው።
በተለይም የመደማመጥን አስፈላጊነት ከጥንታዊ እሴቶቻችን ጋር አናብበው ያቀረቡበት መንገድ የፖለቲካ ስብራታችንን ለመጠገን ወሳኝ ነው። ለዘመናት የኖርንበትን የአለመደማመጥ ባሕል በመቀየር “ለሰፈሬ ሳይሆን ለኢትዮጵያ” ወደሚል አቃፊ ዕይታ ልንሸጋገር ይገባል።
እያንዳንዱ የፖለቲካም ሆነ የማኅበረሰብ ክፍል ከጠባብ ጥቅም ወጥቶ የሌላውን ስጋት እና ፍላጎት ለማዳመጥ ሲዘጋጅ ብቻ የሀገረ መንግሥቱ ጽናት ይረጋገጣል።
የውስጥ መደማመጥ እና ችግርን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ባሕል ለሀገራዊ ደኅንነት ያለው ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘው ያነሡት “የአሞራዎች” ምሳሌያዊ መግለጫ ነው። በጂኦፖለቲካዊ ስሌት ውስጥ የውጭ ኃይሎች በቀጥታ ከማጥቃት ይልቅ የውስጥ የፖለቲካ ስንጥቆችን መጠቀሚያ ማድረግ ይመርጣሉ።
ውስጣዊ አንድነታችንን በውይይት ስናጸና በሀገራችን ላይ ለማንዣበብ የሚሞክሩ የውጭ ኃይሎች የመግቢያ ቀዳዳ ያጣሉ። ስለዚህም ምክክሩ የማይተካ የመጀመሪያው የደኅንነት መከላከያ ግንባችን ነው።
ከዚህ ባለፈ ይህ መድረክ ከተለመዱት የፖለቲካ ድርድሮች የሚለይበት ትልቁ ምሰሶ ለነገው ትውልድ መሠረት ለመጣል ያለመ መሆኑ ነው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለዛሬ አትምከሩ ለነገ ምከሩ፤ ለራሳችሁ አትምከሩ ለልጆቻችሁ ምከሩ” በማለት ለመላው ተሳታፊ አደራ ያሉት።
ምክክሩ በወቅታዊ የሥልጣን ክፍፍል ላይ እንደሚያተኩረው የፖለቲካ ድርድር ጊዜያዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገ ሳይሆን፣ በመግባባት ለልጆቻችን በምናስረክባት የተረጋጋች ሀገር ላይ ያተኮረ ነው።
አሁን ያሉ ልሂቃንም የትናንት የታሪክ ቁስልን እና የዛሬን ጊዜያዊ ጥቅም ተሻግረው ጸንቶ የሚቆይ ፖለቲካዊ መሠረት ሊጥሉ ይገባል።
ይህ የምክክር ሒደት ከውጭ የመጣ ፍልስፍና ሳይሆን በራሳችን ታሪክ ውስጥ የነበረን የማንነት እሴት የማደስ ሒደት ነው።
በባሕላችን የነበረውን የንግግር፣ የይቅርታ እና የሽምግልና ሥርዓት ከዘመናዊ አስተዳደር ጋር በማቀናጀት ኢትዮጵያን ለማጽናት ከምክክር የተሻለ አማራጭ የለም።
ለዘመናት የተከማቹ ውስብስብ ችግሮችን በአንድ ጀምበር መፍታት ባይቻልም በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መነጋገር መጀመሩ ራሱ የታሪካችንን ስብራት ለመጠገን የተወሰደ ትልቁ እርምጃ ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: