Search

ከዘመን እና ትውልድ ጋር የሚታገለው የከሰረው ቡድን

ዓርብ ሐምሌ 10, 2018 180

የዘመን ፍሰት እንደ ታላቅ የውቅያኖስ ማዕበል ወደፊት እንጂ ወደኋላ ፈጽሞ የማይመለስ፣ ኃያላንን የሚያንበረክክ ጽኑ የተፈጥሮ ዑደት ነው።

ትውልድ ዳግም ወደ ኋላ ተመልሶ አይወለድም፤ የትናንት ነገሥታት፣ የትናንት የተንሸዋረረ የፖለቲካ ዕድል፣ የትናንት የጉልበት እና የጭቆና ዘመን ከነባለቤቶቹ ጋር በትናንት ማኅደር ውስጥ ተዘግቶ አልፏል።

ዛሬ ላይ ቆሞ የትናንትን በረዶ ለማቅለጥ፣ ወይንም የትናንትን ፀሐይ ዳግም ለመሞቅ መሞከር፣ በምናብ ከተፈጠረ ከንቱ ቅዠት ጋር መታገል ነው።

ትውልዱ፣ ዘመኑ፣ ሐሳቡ እና ራዕዩ የራሱ አዲስ መድረክ፣ የራሱ ጊዜ እና የራሱ ኃላፊነት ውስጥ ነው ያለው። ለዚህ ለተቀየረ፣ ለሠለጠነ እና ላደገ አዲስ ዘመን የተፈጠረ፣ የነቃ እና ያወቀ አዲስ ትውልድ አለ።

በሁሉም የዓለማችን ክፍል እንደሚታየው፣ ይህ የዛሬው ዘመናዊ ትውልድ የራሱን ዕጣ ፈንታ በራሱ ይወስናል፤ የራሱን ዘመን በራሱ እጆች ያቃናል እንጂ፣ ትናንትን ያበላሸ መንፈስ እንዲመራው ከቶውንም አይፈቅድም።

በእኛዋ ውድ ኢትዮጵያችን፣ ትናንት ሀገርን ያጣመሙ፣ የሕዝቦችን አብሮነት የገደሉ እና ወንድማማችነትን ያቆሰሉ ጨካኝ መዳፎች፣ የዛሬውን ነፃ ትውልድ ዕጣ ፈንታ እና የነገዋን ብሩህ ሀገር ጉዞ ዳግም ለማጣመም ሲሞክሩ ማየት እጅግ የሚያሳዝን እና የሚያስገርም ክስተት ነው።

የከሰረው፣ ዘመን የተላለፈበት እና ውድቀቱን ማመን ያቃተው የህወሓት ቡድን ትናንትን በትናንት ትዝታ፣ ዛሬን ደግሞ በባዶ ምኞት ውስጥ እየኖረ፣ የደረሰበትን ታሪካዊ እና ሞራላዊ ኪሳራ ለማወራረድ ከዘመን እና ከትውልድ ጋር እልህ አስጨራሽ ግብግብ ውስጥ ይገኛል።

ነገር ግን፣ እውነታው ለሁሉም ግልጽ ነው፤ ዘመን ተላልፎባቸዋል! ማንም ምድራዊ ኃይል ዘመንን፣ ጊዜን እና ትውልድን ተጋፍቶ፣ የተፈጥሮን የለውጥ ሕግ ጥሶ አሸንፎ አያውቅም።

ሁሉም ሰው፣ ሁሉም ፖለቲካዊ ቡድን እና ሁሉም ትውልድ በጊዜ ሰሌዳ ውስጥ የራሱ የሆነ የተወሰነ ዕድል፣ መፈተኛ እና ማለፊያ ጊዜ አለው። የራሱን ዘመን በክፋት ያባከነ፣ አሁን ደግሞ በሌላ አዲስ ትውልድ ጊዜ ላይ ሊቆም የሚያስችለው ምንም ዓይነት ሞራላዊም ሆነ የተፈጥሮ ዕድል የለውም።

የከሰረው ቡድን አብቅቶለታል፤ መክኗል። የራሱን ዘመን በጥፋት፣ በዘረፋ እና በኪሳራ አሳልፏል። ኢትዮጵያን የልዩነት፣ የጥርጣሬ እና የግጭት ማዕከል አድርጎ፣ የሕዝቦቿን ዕንባ እያፈሰሰ፣ ያንን የተሰጠውን ወርቃማ የታሪክ አጋጣሚ አባክኖ አልፏል።

የእሱ ዘመን ያተረፈው ኪሳራ እና ስብራት፣ ዛሬ የዚህኛው ትውልድ የቤት ሥራ ሆኖብናል። ሆኖም ይህ አዲሱ ትውልድ ያንን አሮጌ ስህተት ለማስተካከል እና ሀገርን ከፍ ለማድረግ ሌት ተቀን እየታተረ፣ በጥበብ እየተመካከረ፣ ስብራቶቹን በፍቅር እና በመደመር እሳቤ እየጠገነ ይገኛል።

ይህ የከሰረ ኃይል የራሱን የተሰጠውን ዘመን ቀርጥፎ በልቶ ሲጨርስ፣ የሌላውን ትውልድ ዘመን እና ዕድል ጭምር ለመብላት የቋመጠ ስግብግብ ነው። ነገር ግን፣ ይህንን አጥፊ ሕልሙን እውን ለማድረግ ምንም ዓይነት አቅም የለውም፤ ምክንያቱም የተፈጥሮ ሕግ አይቀሬ እና የማይታጠፍ ነውና፤ የቱንም ያህል ቢታበዩ ጉልበት ይደክማል፣ ይህ ተፈጥሯዊ ነው!

የቱንም ያህል ቢያሴሩ አፍራሽ ሐሳብ ያረጃል፣ ይነቅዛል፣ ይህ ተፈጥሯዊ ነው! አዲሱ ትውልድም አሮጌውን ትውልድ ይተካል፤ ይህም ተፈጥሯዊ ነው! ይህንን ሐቅ መቀበል መረረንም ጣፈጠንም፣ አጣጥመን ልንወስደው የሚገባ አንገብጋቢ የሕይወት እውነታ ነው።

እናም፣ ለእነዚህ ከጊዜ ጋር ለሚላተሙ የጥፋት ኃይሎች የሚሰጠው የመጨረሻው እውነት "ከዘመን ጋር አትታገሉ!" የሚል ነው።

ከዘመን ጋር መታገል በገዛ ፈቃድ ራስን ከማጥፋት እና የታሪክ ጥላሸት ከመሆን የዘለለ ትርፍ አያመጣም። ይህ ዘመን የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ስብራቶች የሚጠግኑ፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን የሰነቁ ታላላቅ ትውልዶች የተነሡበት ብሩህ ዘመን ነው።

በኢትዮጵያ ላይ የተጠነሰሰው የጠላት ሴራ ፈርሷል፤ የከሰረው ቡድን የመጨረሻ ቀናት ደርሰዋል። ኢትዮጵያ ግን በነቃው ትውልድ እጅ የገጠማትን ዕዳ አወራርዳ፣ ትናንትን አርማ እና ነገን ገንብታ፣ በልዕልናዋ ማማ ላይ ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች!

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: