Search

አፍሪካዊ የዕርቅ መንገድ፡ ከኦባሳንጆ የሰላም ፍልስፍና

ዓርብ ሐምሌ 10, 2018 114

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግር የናይጄሪያን የእርስ በርስ ጦርነት አስከፊነት እና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አነጻጽረዋል፡፡

ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እንዳሉት የውጭ ጦርነት አሸናፊ እና ተሸናፊ ሲኖረው የውስጥ ግጭት ግን የሕዝቦችን አብሮ መኖር፣ መስተጋብር እና ማኅበራዊ ትስስር የሚፈታተን ነዉ።

ይህም ማንኛውም የጠብመንጃ መንገድ ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሔን ሊተካ እንደማይችል እና የሀገረ መንግሥት ግንባታ መሰረቱ የተኩስ ድምጽ ማብቃት ብቻ ሳይሆን የልብ መከፈት ጭምር መሆኑን ያመላክታል።

በናይጄሪያው የእርስ በርስ ጦርነት ማብቂያ ላይ የነበራቸውን ተሞክሮ ሲያካፍሉ ጦርነቱ በጥር 1970 በቴክኒክ ደረጃ ቢያበቃም የፖለቲካ ማብቂያ ግን የግድ እንደሚያስፈልገው መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

የቀድሞ አማጺያንን ወደ ሌጎስ ቤተ መንግሠሥት በመጥራት "እንኳን ደህና መጣችሁ" ማለታቸው እና እንደ ጠላት አለመመልከታቸው አፍሪካዊ የዕርቅ እና የይቅርታ እሴት በምን ያህል ጥልቀት ሊተገበር እንደሚችል የሚያሳይ የዲፕሎማሲ ጥበብ ነው።

ይህ "አሸናፊም ተሸናፊም የሌለበት" የሰላም ጉዞ ፍልስፍና ኢትዮጵያ አሁን እያካሄደች ላለው ሀገራዊ ምክክር ትልቅ ሥነ-ልቦናዊ እና ፖለቲካዊ አብነት ነው።

የፖለቲካ ውድቀት ያመጣውን ጦርነት በፖለቲካዊ የጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሔ ማከም እንዳለበት የሚያምኑት ኦባሳንጆ፣ ብዝሃነትን መሰረት ያደረገ ሀገራዊ ምክክር የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የጀርባ አጥንቶች መሆናቸውን በናይጄሪያው ሞዴል አስረግጠዋል።

ይህም ሂደት የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመከላከል ሀገራዊ ችግሮችን በሀገር በቀል አቅም እና በውይይት የመፍታት አቅምን ያጎለብታል።

ከፖለቲካዊው መረጋጋት ጎን ለጎን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ ውስጥ ያዩት ትልቁ ተስፋ የኢኮኖሚ አቅም መሆኑን አልሸሸጉም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(/) ከሦስት ዓመታት በፊት ያስቀመጡት በስንዴ ራስን የመቻል ራዕይ ዛሬ ላይ ተሳክቶ ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ጭምር መትረፍ መቻሏ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የምግብ ጎተራ የመሆን ትልቅ እምቅ አቅም እንዳላት በተጨባጭ ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

ይህ በግብርናው ዘርፍ የታየው ስኬት ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።

በተለይም 2018 በጀት ዓመት 10.2 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ መተንበዩ ሀገራችን ከፖለቲካዊ መረጋጋቱ ጎን ለጎን የምትገነባው ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት እንዳላት በግልጽ ያሳያል።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤዉ ስኬታማነት ይህንን እምቅ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ ቁልፍ መሰረት በመሆን ያገለግላል።

የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ብዝኃነት፣ የሰው ኃይል እና ታታሪ ሕዝብ በአንድነት ሲቀናጁ፣ ሀገራችን የተጋረጡባትን ፈተናዎች ተሻግራ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በአህጉሪቱ ጠንካራ፣ አንድነቷ የተጠበቀና መሪ ሀገር የመሆን ታሪካዊ ኃላፊነቷን መወጣት እንደምትችል የኦባሳንጆ ንግግር ጥልቅ መልዕክት አስተላልፏል።

በበረከት ሽመልስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: