Search

የትግራይ ሕዝብ ዘላቂ መፍትሄና ሰላም የሚረጋገጠው በሰከነ ውይይት እንጂ በጦርነት አይደለም - አቶ ጌታቸው ረዳ

ቅዳሜ ሐምሌ 11, 2018 175

 

ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚፈፅመውን አፈና እና ጭቆና የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እየተካሄደ ይገኛል።

አቶ ጌታቸው ረዳ በሰልፉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የትግራይ ሕዝብ ዘላቂ መፍትሄና ሰላም የሚረጋገጠው በሰከነ ውይይት እንጂ በጦርነት አለመሆኑን አስምረውበታል።

በትግራይ ክልል የሚገኙ እናቶች እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ህጻናት ልጆቻቸውን እየተነጠቁና እየተገፈፉ ያሉበትን እውነታ ያነሱት አቶ ጌታቸው፣ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት ሰላም መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥና በትግራይ የሚገኙ ንጹሃን ዜጎችን ከማንኛውም ስጋት የመጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት የፌዴራል መንግሥት፣ ይህንን ድርሻውን በንቃት ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ትግራይ በሙሉ አቅሟ የፌዴሬሽኑ ንቁ አካል የምትሆንበት እና ከሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ጋር ያላት ትስስር ይበልጥ የሚጠነክርበት ጊዜ እንዲመጣ ሁሉም ወገን በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በዚህ የሰላም ሂደት ውስጥ የፌዴራል መንግሥት እስካሁን ወደ አላስፈላጊ ግጭቶች ላለመግባት ያሳየው ከፍተኛ ትዕግስትና አስተዋይነት እጅግ የሚደነቅ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህ አዎንታዊ እና ሰላማዊ ትዕግስት ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከአፋኙ ቡድን ጋር በመሆን አሁንም በክልሉ የጦርነትና የጥፋት ከበሮ ለመደለቅ ከሚሞክረው ኃይል ጀርባ ያሉ አካላት በሙሉ ለዚህ አጥፊ ስብስብ ድጋፍ መስጠታቸውን እንዲያቆሙም አቶ ጌታቸው ረዳ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ የጸጥታ ኃይሎችና መላው ሕዝብ ለዚህ የጥፋት ቡድን ያላቸውን እምቢተኝነት በተግባር እንዲያሳዩ እና ለሰላማዊው አማራጭ ቅድሚያ እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የትግራይ ሕዝብ የወደፊት እጣ ፈንታ ከጦርነት አዙሪት መውጣትና በጋራ ልማት ላይ ማተኮር ብቻ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በሃና ምንዳሁን

 

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: