በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ያለመደማመጥ ፖለቲካ ሀገራችንን ዋጋ ሲያስከፍላት የኖረ ነው። ሀገራችን ላለፉት በርካታ ዐሥርት ዓመታት በፖለቲካዊ ውጥንቅጥ እና መጠላለፍ ፈተናዎች ተፈራርቀውባታል። በርካታ ዕድሎችም አምልጠዋታል።
እነዚህን የዘመናት የፖለቲካ ቁስሎች ለማከም እና የላላውን የማኅበራዊ ትሥሥር ክር ለማጥበቅ፣ ሁሉን አቀፍ ውይይት እና ብሔራዊ ዕርቅ እንዲወርድ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች እና ማኅበረሰቦች ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ከለውጡ በፊት በነበረው ሥርዓት መንግሥት ለእነዚህ የሕዝብ እና የልሂቃን ጥሪዎች የሰጠው ምላሽ፣ በሀገራችን የነበሩትን መዋቅራዊ የፖለቲካ ስብራቶች ሙሉ በሙሉ የካደ ነበር።
እንዲያውም ጥያቄውን በማጣጣል "ማን ከማን ጋር ተጣላ?" የሚል ፌዝ እና ንቀት የተሞላበት ምላሽ ሲሰጥበት ቆይቷል።
ይህ ዓይነቱ ግትር አቋም እና በጥርጣሬ እንዲሁም በከፋፍለህ ግዛ ስልት ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ መዋቅር፣ የሕዝብ ተቃውሞን በማባባስ በመጨረሻም ለሀገራዊ ለውጥ ዋነኛ መነሻ ለመሆን በቅቷል።
ዛሬ ላይ ያ ሕዝብን የከፋፈለ እና ያገለለ ሥርዓት ተቀይሮ በመንግሥት አነሣሽነት ታሪካዊ የፖለቲካ ስብራቶችን ከመሠረቱ ለመጠገን የሚያስችል አዲስ ሀገራዊ የምክክር ምዕራፍ ተጀምሯል።
ለዘመናት የቆዩ የፖለቲካ ውዝግቦችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በማለም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደ ሥራ ገብቷል።
ኮሚሽኑ ሒደቱን አካታች፣ አሳታፊ እና ግልጽ ለማድረግ ወደ ሕዝብ መሠረት በመውረድ አጀንዳዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል።
የተሰበሰቡት አጀንዳዎችም በጥንቃቄ ተበጥረው እና ተደራጅተው ወደ ስምንት ዋና ዋና የትኩረት ነጥቦች በመመደብ ለዋናው የምክክር ጉባኤ ቀርበዋል።
ኢትዮጵያ አሁን እያካሄደች ያለው ሀገራዊ ምክክር ዋነኛ የለውጥ እና የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብን ያማከለ መሆኑ የነበርንበትን የፖለቲካ ባህል የቀየረ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮች መኖራቸው የማይካድ ሐቅ ሲሆን፣ በእነዚህ ውዝግቦች ምክንያት ለዘመናት የጉዳቱ ሰለባ ሆኖ የቆየው ደግሞ ይኸው ሕዝብ ነው።
ልሂቃን ተሰብስበው ሥልጣን ሲከፋፈሉበት፣ ጥቅም ሲቀርባቸው ደግሞ በስሙ የሚጣሉበት ይህ ሕዝብ የራሱ የሆነ የቆየ፣ የዳበረ የውይይት እና የእርቅ ሥርዓት ያካበተ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ የነገ የጋራ ዕጣ ፈንታውን እና ለሀገር የሚጠቅመውን ነጥብ በነፃነት እንዲወያይ አጀንዳውን በእጁ አስገብቷል።
ይህ ሀገራዊ ምክክር በተሳካ ሁኔታ ሲጠናቀቅ ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጀምሮ መታረም ያለባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ሁሉ በሕዝብ ቀጥተኛ ፍላጎት እና ውሳኔ ብቻ ታርመው አዲስ የጋራ ማኅበራዊ ውል የሚታሰርበት ይሆናል።
ይህ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ዘላቂ ጥንካሬ እና ለሕዝቦች አንድነት ብቸኛው ፍቱን መፍትሔ ነው። በዚህ አካታች መንገድ ማንም ወደ ኋላ የሚተው ሳይኖር ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሀገሩ ባለቤት መሆኑን በተግባር ያረጋግጣል።
ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ወገኖች ይህን የሰላም እና የውይይት መንገድ አይፈልጉትም።
የመጀመሪያዎቹ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተገዝተው የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው የሚሸጡት ናቸው። እነዚህ ወገኖች ዴሞክራሲያዊ ሒደትን ወደ ጎን በመተው በአቋራጭ ሥልጣን ተቆጣጥረው ለከፋዮቻቸው የውጭ ኃይሎች ታሪካዊ ውለታ መዋል ይፈልጋሉ።
በዚህ ዓይነቱ ሀገርን የካደ መንገድ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትነጠል እና የባሕር በር አልባ እንድትሆን መደረጉን ይህ ትውልድ በአካል ያየው እና የታዘበው ታሪካዊ ጠባሳ ነው።
ሁለተኛው ወገን ደግሞ፣ ለሕዝብ እና ለሀገር ኑሮ መሻሻል የሚያመጣ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወይም አማራጭ ፖሊሲ ሳይኖራቸው ሥልጣንን ብቻ በብርቱ የሚመኙት ናቸው። እነዚህ ወገኖች ሕዝብ የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ በሚሆንበት ዴሞክራሲያዊ መድረክ ላይ ቦታ እንደሌላቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ሁልጊዜም በአቋራጭ እና በኃይል ሥልጣን ለመጨበጥ ይቋምጣሉ።
ይህ ዓይነቱ ኃላፊነት የጎደለው እና አግላይ አካሔድ ግን ለዘመናት ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን እጅግ ከባድ ዋጋ ሲያስከፍል የነበረ "ዜሮ ድምር" የፖለቲካ ጨዋታ ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ የተጀመረውም ይህንን አጥፊ ልማድ በማስወገድ አሸናፊ እና ተሸናፊ የሌለበትን የጋራ መግባባት ለመፍጠር ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ የአሁኑ ትውልድ ሀገሩን ከፈተና ለማሻገር ያገኘው ወርቃማ እና ታሪካዊ ዕድል ነው። በመሆኑም፣ በ"ማን ከማን ጋር ተጣላ?" ፌዝ የባከኑትን ዓመታት ለመካካስ፣ መላው ኢትዮጵያውያን በዚህ አካታች ሒደት ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የተሻለች እና የተባበረች ኢትዮጵያን ለመገንባት ቆርጠው ተነሥተዋል።
የነገዋ ኢትዮጵያ ሰላም እና ብልጽግና የሚረጋገጠው በጠመንጃ አፈሙዝ ወይም በልሂቃን ሴራ ሳይሆን በሕዝቧ ነፃ ውይይት፣ ይቅርታ እና የጋራ መግባባት ብቻ ነው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: