Search

አዲሱ የዓለም የእህል ገበያ እና የኢትዮጵያ ስንዴ የሚቀዳጀው ታሪካዊ ድል

ሰኞ ሐምሌ 13, 2018 106

የዓለምን የኢኮኖሚ ምህዋር ሊቀይር የተቃረበው ግዙፉ የብሪክስ የእህል ግብይት መድረክ እውን መሆን ሲቃረብ፣ ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ በግብርናው አብዮት እያበበች ለምትገኘው ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አዲስ የወርቅ ዕድሎችን ይዞ እየመጣ ነው?

ዓለም አቀፉ የንግድ ሥርዓት ከምዕራባውያን አገዛዝ እና ከዶላር ጥገኝነት ብቻ ተላቆ በራሱ የዋጋ ተመን ሊመራ በዝግጅት ላይ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ የስንዴ ኤክስፖርት ጉዞ ከዚህ አዲስ ዓለም አቀፍ ማዕበል ጋር እንዴት ይተሳሰራል?

ሩሲያ፣ ሕንድ እና ብራዚልን ጨምሮ የዓለምን የእህል ምርትና ፍጆታ 44 በመቶ የሚሸፍኑት የብሪክስ ሀገራት፣ የራሳቸውን ራሱን የቻለ የዋጋ ተመን፣ ከዶላር ነፃ የሆነ የንግድ ልውውጥ እና አስተማማኝ የምግብ ዋስትና ማዕቀፍ ለመፍጠር እያፋጠኑት ያለው ዝግጅት ዓለምን ትኩረት ስቧል።

ከመጀመሪያው ጀምሮ በሩሲያ አነሳሽነት እና በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ድጋፍ የጀመረው ይህ ግዙፍ የሸቀጦች መለዋወጫ መድረክ፣ ከ1 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚገመት ዓመታዊ የግብርና ምርቶች ንግድ የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ አውታር ለመሆን ተቃርቧል።

ይህ ማለት አዳጊ ሀገራት ከግምታዊ የዋጋ ንረትና ከገበያ ማጭበርበር ተጠብቀው በፍትሐዊነት የሚገበዩበት አዲስ ዘመን መባቻ ላይ እንገኛለን ማለት ነው።

ይህ እጅግ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ለውጥ ለኢትዮጵያ አስገራሚ ፋይዳ አለው። ሀገራችን በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ታሪካዊ ስኬት አስመዝግባለች።

በዚህም የውስጥ ፍላጎቷን አሟልታ ወደ ውጭ ሀገራት መላክ የጀመረችበት ወቅት ከዚህ አዲስ የብሪክስ ገበያ መፈጠር ጋር በትክክል መገጣጠሙ ትልቅ ዕድል ነው።

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ስንዴ በገበያ መዋዥቅና ፖለቲካዊ ቅድመ-ሁኔታዎች ሳትገደብ፣ በአዲሱ መድረክ በኩል ፍትሐዊና የተረጋገጠ ዓለም አቀፍ ዋጋ እንድታገኝ የሚያስችል ሰፊ በር ይከፈታል።

ከዚህም በላይ ግብይቱ በአባል ሀገራት ብሔራዊ ገንዘቦች የሚፈጸም በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ከዶላር እጥረት ጫና ተላቃ የኤክስፖርት ምርቶቿን ከብሪክስ ሀገራት ጋር በቀጥታ የገንዘብ ልውውጥ ሥርዓት ለመገበያየት የሚያስችል አቅም ትጎናፀፋለች።

መድረኩ ከሚያንቀሳቅሰው ከ1 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ንግድ ጋር ተያይዞ፣ ሀገራችን የስንዴና የግብርና ምርቶቿን በብቃት ለማጓጓዝ የሚያስችላትን የቀጣናዊ  ሎጂስቲክስ፣ የጋራ መጋዘኖችና የወደብ ትስስር መሠረተ-ልማቶችን ከባልደረባ ሀገራት ጋር በጋራ የማሳደግ ዕድሏ እጅግ የሰፋ ነው።

በተለይም ሕንድ የ2026 የብሪክስ ሊቀ-መንበርነቷን ይዛ በምግብ ዋስትና እና በግብርና ትብብር ላይ በልዩ ትኩረት እየሰራች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በአፍሪካ ያላትን የስንዴ አምራችነት አቅም ይበልጥ በማጎልበት በቀጣናው የምግብ ዋስትና መሪነቷን ማረጋገጥ ትችላለች።

የግሎባል ሳውዝ ሀገራትን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጠው ይህ አዲሱ የእህል ግብይት መድረክ፣ የኢትዮጵያን የግብርና ብልጽግና እና የውጭ ምንዛሬ ገቢ በዘላቂነት ለማሳደግ ታሪካዊ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

የኢትዮጵያ ስንዴ ዛሬ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እያሳየ ያለው አበረታች ጉዞ፣ ከዚህ ግዙፍ የብሪክስ አውታር ጋር ተቀናጅቶ የሀገራችንን የኢኮኖሚ ከፍታ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር አሸናፊ እርምጃ ሆኗል።

በሰለሞን ገዳ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: