Search

የአረንጓዴ ዐሻራ ጥሪ ለነገዋ ኢትዮጵያ

ሰኞ ሐምሌ 13, 2018 129

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የተራቆተ መሬትን መልሶ ለማልማት የጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዘንድሮም በታላቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ መካሄዱን ቀጥሏል።

ይህ ዘመቻ የሀገርን ኅልውና የማስቀጠል እና ለተተኪው ትውልድ ለምለምና ምቹ ሀገር የማስረከብ ትልቅ የሀገራዊ ራዕይ ነፀብራቅ ነው።

የዘንድሮው “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሐሳብ የተጀመረው መርሐ ግብሩ ካለፉት ዓመታት ልምዶች በመነሳት በበለጠ ጥራት፣ ዝግጅት እና ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ ይገኛል።

ቀደም ባሉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ረገድ የተገኙ ስኬቶች እና የታዩ ክፍተቶች ተገምግመው፣ ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞች የመፅደቅ ዕድላቸው ከፍተኛ እንዲሆንም ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል።

እያንዳንዱ ክልል እና ዞን ከሥነ-ምህዳሩ ጋር የሚስማሙ፣ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ እና ለአፈር ጥበቃ ጠቃሚ የሆኑ የዛፍ ዝርያዎችን ለይተው እየተከሉ ይገኛሉ።

መትከል ብቻ ሳይሆን ማፅደቅ የሚለው መርህ ይበልጥ በባለቤትነት ስሜት እንዲተገበር፣ እያንዳንዱ የተተከለ ችግኝ የክትትልና እንክብካቤ ሥርዓት ተበጅቶለታል።

የዘንድሮው መርሐ ግብር የአካባቢ ጥበቃን ብቻ ሳይሆን፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያደረገ ነው።

በመሆኑም በመርሐ ግብሩ ከተተከሉ ችግኞች መካከል ከፍተኛ ቁጥር የሚይዙት የፍራፍሬ ተክል የሆኑት እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ እና ቡና ያሉ ለገበያ የሚሆኑ እና የቤተሰብን አመጋገብ ሥርዓት የሚያሻሽሉ የኑሮ ማሻሻያ ተክሎች በስፋት ተካትተዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ትልቁ ስኬት መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ዓላማ ማስተሳሰሩ ሲሆን፣ ከህፃናት እስከ አዛውንት፣ ከመንግሥት ሠራተኛ እስከ አርሶ አደር፣ የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶች በአንድነት ዐሻራቸውን እያኖሩ ይገኛሉ።

ይህ ንቅናቄ በተለይም በወጣቱ ትውልድ ዘንድ ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን ግንዛቤ የሚያሳድግ እና ተፈጥሮን የመንከባከብ ባህልን የሚያሰርፅ ትልቅ መርሐ ግብር ሆኗል።

አረንጓዴ ዐሻራችንን ማሳረፍ ዛሬ ለምናገኘው ጥላ ብቻ ሳይሆን፣ ነገ ልጆቻችን በነፃነት ለሚተነፍሱት አየር እና ለሚጠጡት ንፁህ ውኃ ዋስትና መስጠት ነው። ሁላችንም ዐሻራችንን በማሳረፍ ታሪክ እንሥራ!

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: