በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ማዕበል ውስጥ የዓለም የቴክኖሎጂ ምህዋር በፍጥነት እየተቀየረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ አፍሪካን በዲጂታል የዕድገት ጎዳና እየቀየረ ያለው ትልቁ ምስጢር የት ይሆን?
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) የብሪክስ ፕላስ አገራትን የዲጂታል ዝግጁነት ይፋ ሲያደርግ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው የስማርት ማኑፋክቸሪንግ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዋና ማዕከል ለመሆን ያላት አቅም ዓለምን እያስገረመ ይገኛል።
የዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች እና የላቁ የዲጂታል ማኑፋክቸሪንግ ማዕከላት የደም ዝውውር አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው የኃይል አቅርቦት መሆኑ ይታወቃል፤ በዚህ ረገድ ደግሞ ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው ጉዞ ወደር የለውም።
የአፍሪካ ታላቁ የኃይል ማማ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ለዘመናዊ ፋብሪካዎች የሚሆን ንጹህ፣ ታዳሽና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በብዛት የሚገኝበት አዲስ የብልጽግና ምዕራፍ ተከፍቷል።
ይህ ግዙፍ መሠረተ-ልማት የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ አውታሮችን ያለ ምንም መቆራረጥ በመመገብ፣ ሀገራችንን በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ የኢንዱስትሪ መዳረሻ እንደሚያደርጋት የብሪክስ ጉዳይ ተንታኞች በሰፊው እያመኑበት ይገኛሉ።
ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ የወደፊት የዲጂታል ማኑፋክቸሪንግና የስማርት ኢንዱስትሪ ዘርፎችን ይበልጥ ለማነቃቃት የኃይል አማራጮቿን በስፋት ለማስፋት የወሰነችው ታሪካዊ ውሳኔ በግሎባል ሳውዝ መድረክ ላይ ወደ ልዩ የቴክኖሎጂ የበላይነት የሚያሸጋግራት ትልቅ ምዕራፍ ነው።
የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ልማት ለመጠቀም የተደረሰው ቁርጠኛ ውሳኔ የላቁ የዲጂታል ምርት ቴክኖሎጂዎችን፣ ግዙፍ የዳታ ማዕከላትን እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚመሩ ስማርት ኢንዱስትሪዎችን በከፍተኛ የደኅንነትና የጥራት ደረጃ ለማንቀሳቀስ ፍጹም አስተማማኝ ዋስትና ይሰጣል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ እና የኒውክሌር ኃይል አማራጭ በጋራ በመቀናጀት፣ ኢትዮጵያ በብሪክስ ፕላስ “የአዲሱ ኢንዱስትሪ አብዮት አጋርነት” ማዕቀፍ የሚቀርቡላትን የ5G መሠረተ-ልማት፣ የክህሎት ማጠናከሪያ ፕሮግራሞችና የSTEM ትምህርት ዕድሎች በተሟላ አቅም እንድትጠቀም ምቹ የኢኮኖሚ ምኅዳር ይፈጥሩላታል።
በአባል ሀገራቱ ትብብርና በሀገር በቀል የኃይል አብዮቶች የታገዘችው ኢትዮጵያ፣ የዲጂታል ዝግጁነቷን ወደ ላቀ ምዕራፍ በማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በማዘመን እና በቀጣናው የአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ግንባር ቀደም ፋና ወጊ በመሆን ወደፊት እየገሰገሰች ትገኛለች።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: