Search

ኢትዮጵያን ከተፈጥሮዋ የማራቅ የዘመናት ሴራ

ሰኞ ሐምሌ 13, 2018 90

የዘመናት ታሪክ ሲገለጥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር ቀጣና የነበራት የገዘፈ ስፍራ ሁሌም ደምቆ ይታያል። ተፈጥሮ ያደለቻትን ፀጋ፣ የታሪክ አጋጣሚ የሰጣትን ጂኦግራፊያዊ ቁልፍነትና የውሃ ሉዓላዊነት ይዛ፣ የጥንቷ አክሱም ስልጣኔ ወራሽ የሆነችው ሀገራችን፣ የተፈጥሮ መብቷን ለማረጋገጥ ያሳለፈችው ጉዞ ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም።

ሀገራችን የረጅም ዘመን የባሕር በር ባለቤት፣ የዓባይና ታላላቅ ወንዞች እናት እንዲሁም የቀጣናው የሰላም ዋልታ ብትሆንም፣ ሀብቷን እንዳትጠቀም ከላይም ከታችም ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ሲደቀኑባት ኖረዋል። ውበቷንና አቅሟን የቅናት ምንጭ ያደረጉ ታሪካዊ ጠላቶች፣ ኢትዮጵያ በራሷ ፀጋ እንዳትኮራና በቀጣናው ያላትን የተፈጥሮ መብት እንዳታረጋግጥ የሸረቡት ሴራ እጅግ ጥልቅና ዘርፈ ብዙ ነበር።

በተለይም በ18ኛው እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያን የየብስ እስረኛ ለማድረግና ከሁለቱ ወሳኝ የውሃ ሀብቶቿ (ከዓባይ እና ከቀይ ባሕር) ለማራቅ የተቀነባበረው ሴራ እጅግ መራራ ነበር። የግብፅ የከዲቭ ኢስማኤል ፓሻ አስተዳደር ኢትዮጵያን አዳክሞ የዓባይን ምንጭና የቀይ ባሕርን ጠረፍ ለመቆጣጠር ባደረገው ዘመቻ፣ እንደ ቨርነር ሙንዚንገር ያሉ የውጭ ቅጥረኞችን፣ ወራሪዎችን እና ጀብደኞችን በመላክ ሀገራችን ከላይም ከታችም በከበባ ለማንበርከክ ሞክሯል።

ሙንዚንገር እና መሰሎቹ የባሕር በራችንን በመዝጋት፣ የውስጥ ሹማምንትን በማባበልና በማጋጨት፣ ኢትዮጵያን በድህነት አዙሪት ውስጥ ለማስቀረት ሞክረው ነበር። ምንም እንኳን ይህ የጥፋት ሴራ በጉንደትና በጉራዕ የጀግኖች አባቶቻችን ክንድ የተሰበረ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን ከተፈጥሮዋ የማራቁ የሴራ ጠባሳ ግን ቅርፁን እየቀያየረ ለዘመናት ዘልቋል።

ይህ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ሀብቷን እንዳትጠቀም የማድረግ ትንቅንቅ ትናንት አብቅቶ ዛሬ አልቆመም። ዓባይን ጠቅልሎ ለመዋጥ የሚያልሙ ኃይሎች፣ ኢትዮጵያ የራሷን ውሃ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት ሲነፍጓት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ቀይ ባሕርን የብቻቸው ሐይቅ ለማድረግ የሚቋምጡ አካላት፣ ሀገራችንን ከባሕር በሯ በማራቅ አንገቷን ለማስደፋት ተግተዋል።

እነዚህ ኃይሎች በራሳቸው አቅም ፊት ለፊት መጋፈጥ ሲያቅታቸው፣ የውስጥ ባንዳዎችን በመመልመልና የውክልና ጦርነቶችን በማቀጣጠል የዜሮ ድምር ፖለቲካቸውን ሲያራምዱ ኖረዋል። ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጵያ የፀና መንፈስ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ እውን በማድረግ የዓባይን ሉዓላዊ መብት በተግባር አስመልሷል። ይህ ግድብ የሙንዚንገርን ርዝራዦች ሟርት ያከሸፈና ተፈጥሮ ያደላትን ፀጋ ለልጆቿ ብርሃን ያደረገ የታሪክ ሐውልት ነው።

ከዚህ የዓባይ የውሃ ሉዓላዊነት ድል ባሻገር፣ የዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የጂኦ-ፖለቲካዊ መብት በድጋሚ ለማረጋገጥ በታላቅ ታሪካዊ ትግል ውስጥ ይገኛል። ዛሬ ላይ በቀይ ባሕር ዙሪያ እየተደረገ ያለው የዲፕሎማሲ ትንቅንቅ የዚሁ የዘመናት ትግል ቀጣይ ምዕራፍ ነው።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትና እጅግ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለች ሀገር፣ ከቀይ ባሕር ተገልላ ልትኖር እንደማትችል የዘመኑ ትውልድ በፅኑ ተገንዝቧል። የባሕር በር ባለቤትነት መብቷን በተመለከተ ያነሳችው ጥያቄ፣ በታሪክ፣ በሕግና በአስገዳጅ የኢኮኖሚ ትስስር ላይ የተመሰረተ ነው። ይህንን የውሃና የባሕር ሉዓላዊነት መብቷን በሰላማዊ፣ በምክንያታዊነትና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርታ፣ የትናንቱን የሴራ እስራት ለመበጠስ በቁርጠኝነት ተነስታለች።

ጠላቶች "ተዳከመች፣ ተበታተነች" ብለው ሲያስቡ፣ ኢትዮጵያ ግን የዲፕሎማሲ አድማሷን በማስፋትና የውስጥ ባንዳዎችን ሴራ እያመከነች የጥፋት ወጥመዱን በጥበብ እየፈታችው ትገኛለች። የውጭ ኃይሎች የገመዱባትን የጥገኝነት ገመድ በጥሳ፣ የተፈጥሮ መብቷን በማስከበር በቀጣናው የሰላምና የኢኮኖሚ ትስስር ማዕከልነቷን ዳግም እያረጋገጠች ነው።

ታሪካዊ ጠላቶቿ የቱንም ያህል የጥፋት ጥምረት ቢፈጥሩም፣ ኢትዮጵያ የልጆቿን አንድነት ጋሻ አድርጋ፣ ከዓባይ እስከ ቀይ ባሕር የተዘረጋውን የተፈጥሮ መብቷን አስከብራ በድል ጎዳና መገስገሷን አታቆምም። በታሪክ ማህደር እንደተፃፈው ሁሉ፣ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን ለሕዝቦቿ ብልፅግና ማዋሏና ሉዓላዊነቷን ማረጋገጧ የማይቀለበስ እውነት ሆኗል።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: