Search

የሴራው ድር፣ የስበት ማዕከልና የኢትዮጵያ መነሳት

ሰኞ ሐምሌ 13, 2018 93

የኢትዮጵያ ታሪክ ገጾች በጀግንነት፣ በአልበገሬነትና በነጻነት ደማቅ ቀለማት ያሸበረቁ ቢሆኑም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከውጭ ጠላቶችና ከውስጥ ባንዳዎች ጋር የተደረጉ የዘመናት የመረረ ትግሎች ማሳያ ናቸው። ከእነዚህ ታሪካዊ ጠላቶች መካከል፣ የሴራው ዋናው አንገት፣ የበሽታውና የጥፋቱ ስር መሰረት በመሆን ለዘመናት የዘለቀችው ግብጽ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። 

የግብጽ ኢትዮጵያን የማዳከም ህልም የትናንትና የዛሬ የድንገቴ ክስተት ሳይሆን፣ ከጥንት ጀምሮ የተወጠነ፣ ዓባይንና የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት በብቸኝነት ለመቆጣጠር ያለመ ጥልቅ ሴራ ነው።

ይህ የጥፋት ተልዕኮ በተለይም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከመሀመድ አሊ ፓሻ፣ ከታላቁ የከዲቭ ዘመነ መንግሥትና ከእስማኤል ፓሻ የቅዠት ዘመን ጀምሮ ይበልጥ ስልታዊና ተቋማዊ መልክ ያዘ። ግብጽ የራሷን ኅልውና በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ብቻ የተመሰረተ በማድረግ፣ ጎረቤት ሱዳንን እንደ መተላለፊያ ድልድይና የጦር ሰፈር በመጠቀም ኢትዮጵያን ለመውረርና ለማዳከም በርካታ ሙከራዎችን አድርጋለች። 

በጉንደትና በጉራዕ ጦርነቶች የተደረጉት ቀጥታ ወረራዎች በተደጋጋሚ በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ክንድ ሲቀለበሱና የእስማኤል ፓሻ ጦር ውርደት ሲከናነብ፣ ግብጽ አቅሟ ኢትዮጵያን ፊት ለፊት መግጠም እንደማይችል ተገነዘበች። ከዚህ ታሪካዊ ሽንፈት በኋላ ስልቷን በመቀየር የረጅም ዘመን የተንኮል መረቧን መዘርጋት ጀመረች።

✅ የ1920ዎቹ የውሃ ፖለቲካና የብሪታንያ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሴራ

ከ1920ዎቹ ጀምሮ የግብጽና የውጭ ኃይሎች ሴራ አዲስ መልክ ያዘ። እንግሊዝ ግብጽንና ሱዳንን በቀኝ ግዛት በያዘችበት ወቅት፣ ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዋ ማምረቻ የሚሆን የጥጥ ተክል በስፋት ለማልማት ዓባይን የብዝበዛዋ ማዕከል አደረገች። ብሪቲሾቹ የእርሻ ማሳዎቻቸውን ለማስፋፋት ሲሉ፣ የውሃው ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በገዛ ሀብቷ ላይ ምንም ዓይነት ግድብ እንዳትገነባና የልማት ሥራ እንዳትሠራ መሰሪ የውሃ ፖለቲካ ቀመሩ። 

የ1929ኙን እና ተከታይ የቅኝ ግዛት የውሃ ስምምነቶችን በማርቀቅ፣ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ መብት የሚጋፉ ኢ-ፍትሃዊ ማዕቀፎችን አቆሙ። ይህ ዘመን ኢትዮጵያ የውሃውን ምንጭ እንዳትጠቀም የመቆጣጠርና በድህነት የማቆየት ሴራ በይፋ የተጀመረበት የታሪክ ምዕራፍ ነበር።

✅ የመክበብ ስትራቴጂ

በዘመናዊው ታሪክ ግብጽ የሴራ አድማሷን በማስፋት የኢትዮጵያን የመክበብ ስትራቴጂ በስፋት ተገበረች። በተለይም የአረብ ሊግን እንደ ፖለቲካዊ መሳርያ በመጠቀም ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲ ለማግለልና ከአረብ ሀገራት ጋር ለማጋጨት ሰፊ ዘመቻ አድርጋለች። 

በኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ወቅትም ሆነ በሶማሊያ ጉዳይ የግብጽ እጅ አጭር አልነበረም። የኢትዮጵያን አንድነት ለመሸርሸር አዳዲስ የውስጥ ተላላኪ ባንዳዎችን በመመልመል፣ የከሸፉ መንግሥታትን (Failed States) እና የደካማ ኃይሎችን ስብስብ በማደራጀት ቀይ ባሕርንና ዓባይ ሸለቆን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ ሰርታለች። ነገር ግን እነዚህ በገንዘብና በጦር መሳሪያ የሚደገፉ አፍራሽ ኃይሎች፣ ከግብጽ በሚሰጣቸው ፖለቲካዊ ፍርፋሪ የሚንቀሳቀሱ እንጂ ለኢትዮጵያ የኅልውና ስጋት ሊሆኑ የሚችሉበት አቅም ፈጽሞ የላቸውም።

✅ የማይበገረው የኢትዮጵያ ልዕልና

እውነታው ግን ከዚህ የግብጽ ከንቱ የሴራ ድር እጅጉን የራቀ ነው። የሴራው ዋናው አንገትና የበሽታው ስር የሆነችው ግብጽ፣ ምንም ያህል ተላላኪዎችን ብታደራጅ፣ የቱንም ያህል በውስጥ ባንዳዎች ብትጠቀም፣ ኢትዮጵያን ማሸነፍ ከቶውንም አትችልም። ኢትዮጵያ ከጠላቶቿ ሴራ በላይ የገዘፈች፣ በማዕበል ውስጥ አልፋ፣ ፈተናዎችን ተቋቁማ ሁልጊዜም ወደ ልዕልናዋ የምትመጣ ታላቅ ሀገር ናት። 

ታሪክ ደጋግሞ እንደሚመሰክረው፣ የግብጽና የተላላኪዎቿ ሴራዊ ሙከራ ሁሉ መጨረሻው ውድቀትና ውርደት ነው። የጠላቶቿ ሴራ በበረታና በረቀቀ ቁጥር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርቆ አሳቢነትና ቁርጠኝነት ይበልጥ እየጠነከረ፣ ወኔውም እየታደሰ ይመጣል።

የኢትዮጵያ ልዕልናና የማይበገር ኃይል የሚመነጨው በቀጥታ ከራሷ ልጆች አቅም፣ ጥበብና የማይናወጥ አንድነት ነው። ልጆቿ በተባበሩና በአንድነት በቆሙ ጊዜ፣ ሊያቆማቸውና ጉዟቸውን ሊገታቸው የሚችል ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ታሪክ ህያው ምስክር ነው። 

የዘመናት ጠላቶቿ ጊዜያዊ እንቅፋት ቢፈጥሩም፣ ኢትዮጵያውያን በእልህ፣ በጽናትና በልምድ በታነጸ አቅም የሀገራቸውን ብልጽግና ከማረጋገጥ ወደኋላ አይሉም። ዓባይ ዛሬ በልጆቹ የጋራ ላብ፣ ደምና ጥረት ተገድቦ ለብርሃንና ለልማት እንደበቃ ሁሉ፣ የነገዋም ኢትዮጵያ ከማንኛውም የጠላት ሴራና ጥቃት ነጻ ሆና በልጆቿ ጥረት ወደ ላቀ ከፍታ ትሸጋገራለች።

የሴራው ዋና አንገት የሆነችው የግብጽ እኩይ አካሄድና ዘመናትን የተሻገረ የተንኮል ፖለቲካ፣ የኢትዮጵያን የሰላምና የዕድገት ጉዞ ለጊዜው ሊያዘገየው ይሞክር ይሆናል እንጂ፣ መቼም ቢሆን ከታሪካዊ ግቧ አያስቀራትም። የኢትዮጵያ ጠላቶች የቱንም ያህል ሌት ተቀን ቢዶልቱ፣ የደካሞችንና የባንዳዎችን ስብስብ ቢያደራጁ፣ ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች በላይ እጅግ ከፍ ብላ የምትታይ፣ ጠላቶቿን ድል ነስታ የዘላለም ሉዓላዊነቷን የምታስጠብቅ፣ በልጆቿ ዕውቀትና ጥበብ የገዘፈች ሀገር ናት።

✅ የዘመናችን ስኬቶች፡- የሴራውን ድር መበጠስ

1.  አዲሱ የዲፕሎማሲ ምዕራፍና የአረብ ሀገራት ትስስር፡- ኢትዮጵያ የግብጽን ሴራ በማክሸፍ ረገድ ትልቁን ድል የተቀዳጀችው በዲፕሎማሲው መስክ ነው። ቀድሞ ግብጽ የአረብ ሊግን በመጠቀም አረቡን ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ለማነሳሳት ትጠቀምበት የነበረውን ስትራቴጂ፣ ኢትዮጵያ ዛሬ በአዲስ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቀይራዋለች። 

አረብ ሀገራትን እንደ ጠላት ከመመልከት ይልቅ፣ በጋራ ተጠቃሚነት፣ በወዳጅነት፣ በቅርርብና በአብሮነት ፖሊሲ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትስስር እየፈጠረች ትገኛለች። ይህ ስልታዊ እርምጃ ግብጽ ኢትዮጵያን ለማግለል የዘረጋችውን የሴራ ድር በመበጠስ፣ ሀገራችን ከተለያዩ የአረብ ሀገራት ጋር ያላትን ወንድማዊና ኢኮኖሚያዊ አጋርነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።

2.  ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና የቀጣናው የጂኦ-ፖለቲካ ኃይል ሽግግር፡- ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቧን በተባበረ የልጆቿ ክንድ ገንብታ ማጠናቀቋ፣ በቀጣናው የነበረውን የጂኦ-ፖለቲካዊ የኃይል ሚዛን (Geopolitical Power Shift) በአስደናቂ ሁኔታ ቀይሮታል።

ግብጽ ለዘመናት በብቸኝነት ስትቆጣጠረው የነበረው የውሃ ፖለቲካና የበላይነት አብቅቷል። ይህ ታላቅ የኃይል ሽግግር ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ያላትን ሉዓላዊ የውሳኔ ሰጪነት መብት በተግባር ያረጋገጠበት ታሪካዊ ድል ነው።

3. ወደ ቀይ ባሕር የተደረገው የቁርጠኝነት ጉዞ፡- የኢትዮጵያ ራዕይ በሕዳሴው ግድብ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። የግብጽን የመክበብና የማፈን ሴራ ሙሉ በሙሉ በመሰባበር፣ ኢትዮጵያ ወደ ተፈጥሯዊ ወሰኗ፣ ወደ ቀይ ባሕር ለመድረስና የባሕር በር ባለቤትነቷን ለማረጋገጥ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ተነስታለች። ይህ እርምጃ ሀገራችን ያላትን ጂኦ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እምቅ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ከመሆኑም በላይ፣ ጠላቶቿ በፈጠሩት ሰው ሠራሽ ማነቆ ሳቢያ ሲደርስባት የነበረውን ጫና የሚያስቀር የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ግስጋሴ ነው።

4.  ተላላኪዎችን የመበተንና ሉዓላዊነትን የማጽናት ኃይል፡- እነዚህን ሁሉ ስኬቶች ለማደናቀፍ ግብጽ ዛሬም አልተኛችም። በየጊዜው እንደ ከሸፈው ህወሓት  ያሉ የውስጥ ተላላኪዎችን በማደራጀት እንዲሁም በቀጣናው የሚገኙ የከሸፉ መንግሥታትን  በመሳሪያነት በመጠቀም የኢትዮጵያን አቅም ለመበታተን ጥረቷን አላቆመችም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ አቅሟን በመገንባት፣ የውስጥ ባንዳዎችን ሴራ በማክሸፍና የውጭ አፍራሽ ኃይሎችን በመበተን ሉዓላዊነቷን በጽኑ መሰረት ላይ አስቀምጣ እየተጓዘች ነው። 

የሴራው ድር የስበት ማዕከል የቱንም ያህል ቢረዝም እና ቢወሳሰብ፣ ኢትዮጵያ ዛሬም ነገም ታሸንፋለች!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: