Search

በጅማ ዞን ከ235 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ሰብል

ሰኞ ሐምሌ 13, 2018 103

በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ዘመናዊ የግብርና አሠራርን በመተግበር የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ባለው ሰፊ እንቅስቃሴ፣ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከ235 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ ሰብል መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የበቆሎ ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም የአመራረት ዘዴ እየተጠቀሙ እንደሚገኙ የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ ለዚህ የሚሆን በቂ የግብርና ግብዓት ቀርቦ ጥቅም ላይ መዋሉን አመልክቷል።

በኩታ ገጠም ከለማው ከ235 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ እየተመረተ ያለው የበቆሎ ሰብል ተሰብስቦ እስኪጠናቀቅ ድረስ፣ ለአርሶ አደሮቹ በግብርና ባለሙያዎች አማካኝነት በቂ የቴክኒክ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ተገልጿል።

በዞኑ እየተከናወነ ያለው የተቀናጀ የግብርና ልማት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተመልክቷል።

በወሰኑ አውግቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: