የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን የክረምት እረፍት እና ከፍተኛ ሙቀት ተከትሎ፣ አዲስ አበባ ለቱሪስቶች ተመራጭና ምቹ መዳረሻ እየሆነች መምጣቷን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
ጎብኝዎች ሐሙስ እና አርብን አስታከው በሳምንቱ መጨረሻ ወይም ለረዥም ቀናት እረፍት ወደ ከተማዋ በስፋት እየጎረፉ ሲሆን፣ አዲስ አበባም ይበልጥ ሳቢና ምቹ ሆና የቱሪስቶችን ፍላጎት የሚያሟሉ መሠረተ ልማቶችን በማዘጋጀት ይህንን ታላቅ ዕድል በመጠቀም ላይ ትገኛለች።
ከተማዋ የቱሪስቶችን ፍላጎትና ባህል ያገናዘበ የተቀናጀ መስተንግዶ ለመስጠት የፊት ለፊት መስተንግዶ (Reception) ሠራተኞችና አስተናጋጆች መሰረታዊ የዓረብኛ ቋንቋ ፍላጎቶችን መረዳት የሚያስችላቸውን ዝግጅት አድርጋ ወደ ሥራ አስገብታለች።
ከዚህም ባሻገር እንደ የቤተሰብ ግላዊነት ያሉ የጎብኝዎቿን የባህል እሴቶች ማክበር ልዩ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ ከሐሙስ እስከ እሁድ የሚቆዩ ልዩ የዋጋ ቅናሾች፣ የቤተሰብ ፓኬጆች እና የሀላል ምግቦች በሆቴሎች የምግብ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተቱ ተደርጓል።
ለክፍያ ካርዶች ምቹ የሆነ የባንክ አሠራርና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ዋይ-ፋይ ማቅረብ መቻሉም አገልግሎቱን ይበልጥ ቀልጣፋ አድርጎታል።
እንደ አንድነት፣ እንጦጦ፣ ወዳጅነት ፓርክና የሳይንስ ሙዚየም ያሉ አዳዲስ እና ነባር መዳረሻዎች የልጆች መጫወቻዎችንና ማራኪ አረንጓዴ ስፍራዎችን በማዘጋጀት ተደራሽነታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድገዋል።
ቱሪስቶች በተለይ ከሰዓት በኋላና ምሽት ላይ መንቀሳቀስ ስለሚመርጡ፣ የምሽት ጉብኝት መርሃ ግብሮች ተቀርጸው የአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ባለሙያዎች ተመድበውላቸዋል።
በትራንስፖርት ዘርፍም የራይድ ታክሲ ማህበራት መተግበሪያዎቻቸውን ዝግጁ በማድረግ፣ ንጹህና የሙቀት መቆጣጠሪያ (ኤርኮንዲሽነር) ያላቸው መኪናዎችን በስፋት እያቀረቡ ይገኛሉ።
ቱሪስቶች በደላሎችና በአጭበርባሪዎች እንዳይበዘብዙ በግልጽ የተቀመጠ የኪሎሜትር ተመን ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ የቅንጦትና የጋራ አውቶቡስ የአውሮፕላን ማረፊያ የትራንስፖርት አገልግሎቶችም ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።
ከደህንነት አኳያ የቱሪስት ፖሊስ አባላት በንቃት እንዲንቀሳቀሱ ከመደረጉም በላይ፣ የጎዳና ላይ የደህንነት ካሜራዎች፣ መብራቶችና ፈጣን የቅሬታ መቀበያ መስመር (Hotline) ተደራጅተዋል።
በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አበባን በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት እያስተዋወቁ ሲሆን፣ የኢ-ቪዛ አገልግሎትም ፈጣንና ቀልጣፋ መሆኑ ተረጋግጧል።
ይህ የተቀናጀ አሠራር ከተማዋ በየዓመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበትና በዓለም አቀፍ መድረክ ገጽታዋ የሚገነባበት ቋሚ የገቢ ምንጭ እየሆነች መምጣቷን ያሳያል።
በመሐመድ ፊጣሞ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: